Get Mystery Box with random crypto!

በተያዘው ሳምንት በኢትዮጲያ አፋር ክልል አንዳንድ ክፍሎችን ጨምሮ በሱዳን እና ኤርትራ ከባድ ዝናብ | Asham TV

በተያዘው ሳምንት በኢትዮጲያ አፋር ክልል አንዳንድ ክፍሎችን ጨምሮ በሱዳን እና ኤርትራ ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ የምስራቅ አፍሪካ የልማት የበይነ መንግስታት (ኢጋድ) አስታወቀ፡፡

አሻም ዜና |ነሀሴ 10፣ 2014 ዓ.ም

ኢጋድ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በምስራቅ፣ በደቡብ እና በምዕራብ ሱዳን፣ በሰሜን-ምእራብ ኤርትራ እና በኢትዮጲያ አፋር ክልል አንዳንድ አከባቢዎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል አሳስቧል፡፡

በሰሜን ሱዳን፣ በምዕራብ ደቡብ ሱዳን፣ በምዕራብ ኬንያ፣ በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ታንዛኒያ ደግሞ ከሚጠበቀው አማካይ የሙቀት መጠን በላይ ሊስተናገድ እንደሚችል ነው የተተነበየው፡፡

በትንበያውም ከነሐሴ 10 - 17 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ በደቡብ ሱዳን እና በሰሜን ምዕራብ ኤርትራ ውስጥ ባሉ ጥቂት ቦታዎች ከ 200 ሚሜ በላይ የሆነ ከባድ ዝናብ ይኖራል ብሎ ተንብዮል፡፡

በመካከለኛ ዝናብ መጠን ከ50-200 ሚሜ የሚደርስ ዝናብ ያገኛቸዋል የተባሉት ደግሞ ከደቡብ እስከ መካከለኛው ሱዳን፣ አብዛኛው የደቡብ ሱዳን ክፍሎች፣ ከመካከለኛው እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ሰሜን ኤርትራ፣ አብዛኛው የኡጋንዳ ክፍሎች እና አንዳንድ የምዕራብ ኬንያ ክፍሎች ናቸው ተብለዋል፡፡

በምስራቅ እና በሰሜን ታንዛኒያ፣ በሩዋንዳ፣ በባህር ዳርቻ እና በመካከለኛው ኬንያ፣ በአብዛኛዎቹ የሶማሊያ ክፍሎች፣ ከመካከለኛው እስከ ሰሜን ሱዳን፣ በደቡብ-ምስራቅ ኢትዮጵያ እና በጅቡቲ ክፍሎች ላይ የሚጠበቀው ቀላል ዝናብ ከ50 ሚሊ ሜትር ያነሰ እንደሆነም ነው የተጠቆመው፡፡

በቡሩንዲ፣ አብዛኛው የታንዛኒያ ክፍል፣ ምስራቃዊ እና ሰሜናዊ ኬንያ፣ ደቡብ-ምስራቅ ኢትዮጵያ እና አንዳንድ የሰሜን ሶማሊያ አካባቢዎች ደረቅ የአየር ፀባይ ያስተናግዳሉ ተብሏል።

በሰሜን ሱዳን፣ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ፣ በጅቡቲ፣ በባሕር ዳርቻ ኤርትራ እና በሰሜን ምዕራብ ጠረፍ ሶማሊያ ላይ ከ32 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆነ የሙቀት መጠን ይጠበቃል።

በሰሜናዊ ሱዳን ክፍሎች ከሚጠበቀው አማካይ የሙቀት መጠን በላይ ሊስተናገድ ይችላል የተባለ ሲሆን ፣ ሄውም በምዕራብ እና ደቡባዊ ሱዳን የሚገኙ አንዳንድ ክፍሎች ብሎም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች ሞቃታማ ሊሆን እንደሚችል የምስራቅ አፍሪካ የልማት የበይነ መንግስታት ድርጅት ኢጋድ ለአሻም በላከላት መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡