Get Mystery Box with random crypto!

ለዚህ ነው ክርስቲያን #ታንቆ_መሞት አይችልም እሚባለው ለምንድን ነው ፦ እራሱን መግደል የማይችለው | የእውነት ሚዛን(ቴቄል)

ለዚህ ነው ክርስቲያን #ታንቆ_መሞት አይችልም እሚባለው ለምንድን ነው ፦ እራሱን መግደል የማይችለው ታንቆም ሆነ መርዝ ጠጥቶ ኤሌትሪክ ጨብጦ ወይም ገደል ተንከባሎ ክርስቲያን እራሱን መግደል የማይችለው የራሱ ስላልሆነ ነው ። እንግዲያውስ የማን ነው ? የእግዚአብሔር ደም የተዋጀ የክርስቶስ በግ ነው ። እንደዚህ ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ ? እኔ የራሴ አይደለሁም ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ !? የራሴ አይደለሁም ያለ ሰው እኔ አሁን የክርስቶስ እቃ ነኝ ብዬ ካሰብኩ ፦ በዚያውም አንድ ክርስቲያን ክርስቲያን የሚባለው ምን ሲያሟላ ነው የሚለውን እያየን እንሔዳለን ። አሁን ይኸ መጽሐፍ የኔ ከሆነ የኔ መጽሐፍ ነው እኔ አስቀምጨዋለሁ እኔ እስከማነሳው እዚሁ ይጠብቃል ማለት ነው ። ክርስቲያን የእግዚአብሔር ዕቃ ከሆነ እግዚአብሔር ወደ ፈለገው እስኪያነሳው ድረስ እግዚአብሔር አስቀመጠው ቦታ የሚኖር ነው ። የክርስቶስ ሕዋስም ከሆነ በክርስቶስ ይኖራል ። አንድ ሃሳብ ልንገራችሁ ፦ እራስ እና አካል አለ ብያችኃለሁ ። እራስ እና አካል በአንድ ላይ እንዲኖሩ የሚያደርጉ ኹለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ ።
ሰው ያለ አፍንጫ መኖር ይችላል።
ያለ ጆሮ መኖር ይችላል።
ያለ እጅም መኖር ይችላል።
ያለ እግርም መኖር ይችላል።
መኖር የማይችላቸው ኹለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ ።
ያለ ደም እና ያለ እስትንፋስ መኖር አይችልም ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ከሆነች ክርስቲያንም የክርስቶስ ሕዋስ ከሆን እነዚህ ሕዋሳት እንዲንቀሳቀሱ ኹለት ነገሮች ያስፈልጓቸዋል ።
#እስትንፋስ እና #ደም
እንደ እስትንፋስ #ስርዓተ_ቤተ_ክርስቲያንና_ጸሎት ።
እንደ ደም ደግሞ #ቅዱስ_ቁርባን ያስፈልገዋል።
አንድ ክርስቲያን ክርስቲያን ተብሎ የሚጠራው በሥርዓት እና በጸሎት ሲኖር እንደገና ደግሞ በቅዱስ ቁርባን ሲኖር ነው ። ለምን አንድ ሕዋስ ደም መውሰድ ካቆመ ይደርቃል ተቆርጦ ይጣላል ። ክርስቲያን መቁረብ ያቆመ ዕለት ሥጋው እና ደሙን አልቀበልም ያለ ዕለት ከክርስቶስ ተቆርጦ የወጣ ነው:። ከኅብረቱ ይጠፋል ማለት ነው ። እስትንፋሱ ሲቋረጥ ሳንባው መተንፈስ ሲያቆም ሰውዬው ሞተ እንደምንለው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ጸሎት እስትንፋስ ነው ።
የተክሊል ስርዓት
የጦም ስርዓት
የስግደት ስርዓት
የጋብቻ ስርዓት
የምንኩስና ስርዓት
የክህነት ስርዓት
የጵጵስና ስርዓት
ማንኛውም ስርዓት አለው ። ስርዓት በእስትንፋስ የተመሰለበት ምክንያት ፦ በመንፈስ ቅዱስ ስለሚመሰል ነው ። ስርዓት የሌላት ቤተክርስቲያን ይላል ቅዱስ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ ስርዓት የሌላት ቤተክርስቲያን እርሷ የክርስቶስ አካል አይደለችም ። ስርዓት የሌለው ክርስቲያን እርሱ ከክርስቶስ ተቆርጦ የወጣ ሕዋስ ነው ። ተቆርጦ የተጣለ ሰንረለት ነው ። በእስትንፋስ የተመሰለው በመንፈስ ቅዱስ ስለሚፈጸም ነው ማለት ነው ። ስለዚህ የክርስቶስ አካላት በክርስቶስ የምንኖር ነን ። ቅዱስ ጳውሎስ ፩ይ ተሰሎንቄ ፩፥፩ ላይ ሲናገር በእግዚአብሔር አባታችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆነችው ለተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን ይላል ። እና ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይኸን ሲተረጉም ምን ይላል ፦ ወዮ በሰይጣን ፈቃድ እየኖሩ በእግዚአብሔር አባታችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተብለው ለሚጠሩ ክርስቲያን ሐፍረትን አፍርላቸዋለሁ ይላል ።
በሰይጣን ፈቃድ እየኖሩ #እየዘፈኑ በክርስቶስ ነን ማለት አይችሉም ።
እየገደሉ በክርስቶስ አምነናል ማለት አይችሉም ። እየጠነቆሉ እየጨፈሩ እየቀሙ በክርስቶስ ነን ማለት አይችሉም ። በእግዚአብሔር አባታችን ማለት ምንኛ ኩራት ነው ።በሚጠፋ በሚሞት በሚያልፍ ንጉሥ ሳይሆን በሕያው እግዚአብሔር ስም የሚጠሩ ክርስቲያኖች ተብለው ይጠራሉ ። መመከቻቸውም ክርስቶስ የሆነ።
በመጨረሻ ክርስቲያኖች ማለት እንደ ክርስቶስ ስለዚህ እዚህ ላይ ክርስቲያን ክርስቲያን ተብሎ የሚጠራው እንደ ክርስቶስ ሲኖር ነው በሚለው እናጠቃልለዋለን ማለት ነው ። ክርስቶስ በሰማይ አባቱ አብ የባህርይ አባቱ ነው እኛም የክርስቶስ የባህርይ አባቱ ለእኛ የጸጋ አባታችን ነው ። የክርስቶስ አባት የባህሪይ አባታችን ከሆነ የክርስቶስ እናት እናታችን ነች ። ማቴዎስ ፲፪፥፵፫ ጀምሮ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር አንድ ሰው መጣና እናትህ እና ወንድሞችህ ይፈልጉሃል አለው ። አይ እናቴስ ማናት ወንድሞቼስ እነማን ናቸው እናቴና ወንድሞቼ የኔን ቃል የሚሰሙ ናቸው ብሎ መለሰ ይለናል ።
እና ሊቃውንቱ ሲተረጉሙት ፦ እናትህና ወንድሞችህ ይጠሩሃል ያለ ሰው ማነው ይሉና ጉባዔ መፍታት የሚፈልግ #ይሁዳ ነው እንጂ ሌላ ማን ይሆናል ይላሉ ። ጉባዔ የሚፈታ ይሁዳ ነው ። ታዲያ እናትና ወንድሞችህ ይፈልጉሃል ሲባል ክርስቶስ እናቱን ነቅፎ ነው እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው ያለ ሲባል ከእናታችሁ ከአባታችሁ ይልቅ ለሰማይ አባት ለሰማይ እናት መንናችሁ ኑሩ አባቴ ሰማያዊ እናቴም ሰማያዊት እርስቴም ሰማያዊ ዘመዶቼም ሰማያውያን ልብሴም ሰማያዊ ምግቤም ሰማያዊ ጫማዬም ሰማያዊ ጋሻዬም ሰማያዊ ሕሊናዬም ሰማያዊ ሕጉም ሰማያዊ ሃይማኖቴም ሰማያዊ ነው በሉ ለማለት ነው እንጂ እናትን ነቅፎስ አይደለም ብሎ ይናገራል ። እናቴና ሞንድሞቼ ለዚህ ነው ተመልከቱ የሰማይ አባት አብጁ ለማለት ነው ።
አንድ መነኩሴ በገዳም ሲኖር ባህታዊ ነው። ሄዱና አባትህኮ ሞተ አሉት ፦ እርሱም አንተ ለምን ትሰድበኛለህ አባቴ የማይሞት የዘላለም ሕያው ነው ብሎ መለሰ። አባትህ ጎንደሬ ነው ጎጃሜ ነው ትግራይ ነው አማራ ኦሮሞ ቤንሻንጉል ጉምዝ ጉራጌ ነው ስትባሉ #ለምን_ትሰድበኛለህ የኔ አባት የዘላለም አባት ነው በሉ እርሱም ሕያው እግዚአብሔር ነው ። የሰማይ አባት ይኑራችሁ ።
ሊቃውንት ሲተረጉሙት ፦ እናቴና ወንድሞቼ ይኸንን ቃሌን የሚሰሙት ናቸው ። ክርስቲያኖች ማለት የክርስቶስ እናቶች የክርስቶስ ወንድሞች የክርስቶስ እኅቶች ማለት ናቸው ። ሰው የክርስቶስ እናት እንዴት ይሆናል ነው እሺ ወንድሞቹስ ይሁኑ እናቱ እንዴት ነው የምንሆነው ነው ስለዚህ ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ እናት ነው ማለት ነው እንዴት? እናቱ ድንግል ማርያም በድንግልና እንደ ጸነሰችው አረጋዊ መንፈሳዊ ከመ ወላዲተ አምላክ ይላል ። እሷ በድንግልና ቅዱስ ገብርኤልን ሰምታ እንደ ጸነሰች ክርስቲያኖች የሕሊናና የእዝነ ነፍስ የእዝነ ሥጋ ድንግልናቸውን ጠብቀው የጆሮአቸውን ድንግልና ጠብቀው ለመናፍቅ ለፍልስፍና ለረከሰ ትምህርት ሳያስደፍሩ ድንግልናቸውን ጠብቀው ለክርስቶስ ሕያው ቃል ብቻ ጆሮአቸውን ከፍተው ቃሉን ሰምተው ከመምህራን ጸንሰው ምግባርን የሚወልዱ ክርስቲያኖች እንደ እናቱ እንደ ድንግል ማርያም የክርስቶስ እናቶቹ ይባላሉ ።