Get Mystery Box with random crypto!

ስለዚህ ተመልከቱ የማይታየው እግዚአብሔር የማይታወቀው እግዚአብሔር በአቅማችን እናውቀው ዘንድ ፀሐይ | የእውነት ሚዛን(ቴቄል)

ስለዚህ ተመልከቱ የማይታየው እግዚአብሔር የማይታወቀው እግዚአብሔር በአቅማችን እናውቀው ዘንድ ፀሐይን ሙቀን ባንጨርስ ለብርድ ያህል ጥቂት እንደምንሞቀው ውቅያኖስን ጠጥተን እንደማንጨርሰው እንኳን ለጥም ያህል ጥቂት እንደምንጠጣው ሁሉ እግዚአብሔርን ጨርሰን ባናውቀውም በፈቀደው መጠን ለልጅነት የሚረባንን እውቀት ስለእርሱ እንድናውቅ ፈቅዶልናል ። ያንን ደግሞ እራሱ ካልተናገረ እራሱ ካልተገለጠ ፍጥረት ስለ እርሱ በመናገር የፈጣሪን ነገር ማወቅ አይቻልም ። ስለዚህ በሐዲስ ኪዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ሥግው ቃል እራሱ እግዚአብሔር የሆነው ቃል እግዚአብሔር ቃል ተገልጦ ስለእራሱ ነገረን ።
ለእግዚአብሔርሰ አልቦ ዘርእዮ ግሙራ አላ ወልድ ዋሕድ ዘሀሎ ውስተ ሕፅነ አቡሁ ውእቱ ነገረነ ።
" እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ ነገረን እንጂ።"
(የዮሐንስ ወንጌል ፩፥፲፰ )
ስለ እግዚአብሔር የሚነግረን ማነው ከተባለ ስለ እግዚአብሔር የሚነገረን እውቀት ትክክል የሚሆነው እግዚአብሔር እራሱ ከነገረን ብቻ ነው ። ስለዚህ ሌሎቹ ሃይማኖቶች ወይም ሌሎቹ የእምነት ድርጅቶች የሚሉት ስለምናመልከው አምላክ በትንቢት ተነግሮናል በራዕይ ተገልጦልናል ነው ። እኛ ግን የምንለው ስለምናመልከው ሕያው አምላክ ስለ ቅዱስ እግዚአብሔር እግዚአብሔር በሥጋ ተገልጦ ነግሮናል ነው ። ለምን ሲባል ፦ እግዚአብሔር ካልተናገረ በቀር ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የሚችል ስለሌለ ። እግዚአብሔር እንዲገለጥ ያደረገውም ስለዚህ ነው ። ስለዚህ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ትክክል ናት የምንለው እራሱ እግዚአብሔር ስለ እራሱ ካልተናገረ በቀር እግዚአብሔርን የሚያውቅ ስለሌለ እግዚአብሔር እራሱ ተገልጧል ብላ የምታምን ይህቺ ቤተክርስቲያን ስለሆነች እግዚአብሔር በልብነቱ በአብ ልብነት ተመክሮ በወልድ ቃልነት ተነግሮ በመንፈስ ቅዱስ ሕያውነት ጸንቶ የተመሰረተ እግዚአብሔር ስሩ የሆነለት ዛፍ ምን ይባላል ክርስትና ተብሎ ይጠራል ። ከክርስቶስ የሚለው ። ይህ ማለት ምን ማለት ነው ክርስቶስ እራስ የሆነላት ክርስቶስ እራስ የሆነለት ቤተክርስቲያን አካል የሆነችለት እሱ ሕዋስ የሆነ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል ። ክርስቶስ እራስ ቤተ ክርስቲያን አካል ምእመናን ሕዋሳት የሆኑላት ይቺ ምን ትባላለች ክርስትና የክርስትና ሃይማኖት የሚባለው እርሱ ነው ። ክርስቲያኖች የሚባሉት ክርስቶስ እራሳቸው ቤተ ክርስቲያን አካላቸው እነሱ ሕዋሳት የሆኑ አንድ ማኅበር ማለት ነው ። ኤፌሶን ፩፥፳፫ ላይ ከክርስቶስ በላይ ሌላ አምላክ የለም አብም አንድ ናቸው በሥልጣን ፤ መንፈስ ቅዱስም አንድ ነው ። ስለዚህ ከክርስቶስ ክርስቶስን እራስ አድርጎ ቤተክርስቲያንን አካል አድርጎ የበቀለ ሕዋስ ማለት ነው ። የክርስቶስ ሕዋስ ማለት ነው ክርስቲያን ። እንደ ጣት እንደ ጥፍር እንደ ዐይን እንደ ጆሮ አንድ እራስ አለ አንድ አንገት አለ አንድ አካል አለ ብዙ ሕዋሳት አሉ ። አንድ እራስ እንዳለ አንድ እግዚአብሔር አለ ። አንድ አንገት እንዳለ አንድ ሃይማኖት አለ ። አንድ አካል እንዳለ አንዲት ቤተ ክርስቲያን አለች ። ብዙ ሕዋሳት እንዳሉ ብዙ ክርስቲያኖች ይኖራሉ ማለት ነው ። ብዙ ክርስቲያኖች መሆናችን ብዙ ሕንጻ አሁን እዚህ የልደታ እዚያ የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲን ቢኖር እንዚህ ሁሉ አንዲት ቤተክርስቲያን ናቸው ። ለምን ፦ ሰው ብዙ ጣት ብዙ ጥፍር ብዙ ጠጉር እያለው ነገር ግን አንድ ሰው ይባላል ። ከክርስቶስ አንድነት የቤተክርስቲያን አንድነት የተመሰረተ ስለሆነ ስለዚህ ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ሕዋስ ማለት ነው።
ሦስተኛ ክርስቲያን ማለት በክርስቶስ ማለት ነው ። በክርስቶስ ማለት በክርስቶስ ስም የተጠራ ማለት ነው ። በክርስቶስ ስም የሚመካ በክርስቶስ ስም የሚመክት ለክርስቶስ ስም የታመነ በክርስቶስ ስም የሚሞት ማለት ነው ። መኃልይ ዘሰሎሞን ፩፥፩ ጀምሮ ስታነቡ ስምህ እንደሚፈስ ዘይት ነው ይላል ። ስምህ እንደሚፈስ ዘይት ነው ማለት ፦ ክርስቶስ የሚለው ስም ክርስቲያን በሚባሉት ላይ እንደ ዘይት ፈሶባቸው ይኖራል ነው ። ስለዚህ ተመልከቱ ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ የስሙ ዙፋን የስሙ ማደሪያዎች የስሙ መጠሪያዎች የስሙ መገለጫዎች ማለት ናቸው ። ስምህ እንደሚፈስ ዘይት ነው እርሱ ክርስቶስ ነው ክርስቶስ የሚለው ስም በውስጣችን በልባችን በራሳችን በመላ ሕይወታችን ላይ ከመኖሩ የተነሳ ክርስቲያኖች ተብለን እንጠራለን ነው ። ስለዚህ ክርስቲያንን ማንሳት ክርስቶንስን ማንሳት ነው ክርስቲያንን መንቀፍ ክርስቶስን መንቀፍ ነው ። በክርስቶስ ስም የከበሩ ማለት ነው ። ዘይት ያረፈበት ሁሉ ያበራል ። በዘይት የተጠረገ ብረት ዝገቱ ይለቅለታል ይጠራል ያበራል ያጥበረብራል ። የክርስቶስ ስም በላያችን ላይ ከማደሩ የተነሳ ለስሙ ታምነን ከመኖራችን የተነሳ በዚህ ምክንያት የጠራን እንሆናለን ማለት ነው ። ስለዚህ በክርስቶስ ስም የተጠራን ማለት ነው ። በስሜ ስለተጠራችሁ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ በክርስቶስ ስም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ይባላሉ ማለት ምን ማለት ነው ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ስም እንኖራለን ይላሉ ። ስሙን ሕይወት መድኃኒት እንደሆነ የሚያምኑ ስሙን እንደ ነቢይ እንደ አማላጅ እንደ ሐዋርያ እንደ መልአክ የሚቆጥሩ ሳይሆኑ ስሙ ሕይወት ነው መድኃኒት ነው ብለው የሚያምኑ ለዚያ ስም የሚሞቱ ትሞታላችሁ ሲባሉ ክርስቶስ ትንሳኤ ነው የሚሉ ትጠፋላችሁ ሲባሉ ክርስቶስ ሕይወቴ ነው የሚሉ ለዚህ ስም ኑረው በዚህ ስም ተጠምቀው በዚህ ስም ከብረው በዚህ ስም መክተው ለዚህ ስም የሚሞቱ እነዚህ ክርስቲያኖች ይባላሉ ። እንደ ክርስቶስ ማለት ነው ። ወይም የክርስቶስ ማለት ነው ። እስኪ የክርስቶስ ከሚለው እንጀምር የክርስቶስ ሕዋስ ነን ብለናል ። የክርስቶስ ከሆን ሰው የራሱ አይደለም ማለት ነው ። ክርስቲያን የራሱ ሁኖ አያውቅም ። እንግዲያ የማነው የክርቶስ ነን ። እምንሞተው ለምንድነው ታዲያ
እምንሞተው
እምንታረደው
እምንቃጠለው
እምንገደለው
እምንሰደደው
ሐብት የምንዘረፈው
ከሀገር የምንሰደደው ለምንድነው የእኛ ስላልሆንን ነው ። የክርስቶስ ስለሆን ለክርስቶስ ሙተን በክርስቶስ ተነስተን ለመኖር ነው ። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ በዋጋ ተገዝታችኃልና የራሳችሁ አይደላችሁም ያለው ። የክርስቲያን አንዱ የጠጉር ዘለላው እንኳን ቢሆን የእግዚአብሔር ደም ተከፍሎበታል ። ይኸን ታውቃላችሁ ?