Get Mystery Box with random crypto!

ወንድሞቹ እኅቶቹ የሚባሉት ደግሞ ፦ ከእናት አባት የተወለደ እኅት ወንድም እንደሚባል አባቱን አብን | የእውነት ሚዛን(ቴቄል)

ወንድሞቹ እኅቶቹ የሚባሉት ደግሞ ፦ ከእናት አባት የተወለደ እኅት ወንድም እንደሚባል አባቱን አብን አባት እናቱን ወላዲተ አምላክን እናት በማድረግ የክርስቶስ ወንድሞች ይባላሉ ። እሱ ብቻም አይደለም ። ክርስቶስን በመከራና በኑሮ የሚመስሉ በሕግ በመከራ በኑሮ የሚመስሉት እንደ ክርስቶስ የሚኖሩ እንነዚህ ክርስቲያኖች ተብለው ይጠራሉ። ማቴዎስ ፲፩፥፳፭ ላይ ከእኔ ተማሩ እኔም የዋህ ቸር በልቤም ትሁት ነኝ ይላል ፦ ስለዚህ ክርስቶስን እያዩ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ይባላሉ ። አሁን ብዙ የእምነት ድርጅቶች አሉ ። በክርስትና ስም ብቻ ከ፴ ሺ በላይ የመጡ አሉ ። ግን እኛ ከእነሱ የምንለየው በምንድን ነው ሲባል ፦ ክርስቶስን እያየን እሱን መስለን በኑሮ እንኖራለን ነው ። ሌሎቹ በአፍ የክርስቶስ ነን ይላሉ ። እኛ ደግሞ በኑሮ እንመስለዋለን ። አባቱን አባት አድርገን በጥምቀት እንወለዳለን ። አባቱን እሱን መንፈስ ቅዱስን አባት አድርገን በጥምቀት እንወለዳለን ። እናቱን ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክን እናት አድርገን በምልጃ በጸጋ ከእርሷ እንወለዳለን ። እርሱ ከድንግል እንደ ተወለደ እኛም ከድንግል ጥምቀት እንወለዳለን ይላል አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ።
ለምን ?፦ እመቤታችን ጌታን ከወለደች በኋላ ማሕተመ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ ሁሉ ጥምቀትም ከባሕሩ ተጠምቀው ከወጡ በኋላ ሰውየው ገብቶ የወጣበት ባህር ጎድጉዶ አይገኝም ። ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወለደ እኛም ከድንግል ጥምቀት እንወለዳለን ።
እንደ ተጠመቀ እንጠመቃለን
እንደ ተሰደደ እንሰደዳለን
እንደ ፆመ እንፆማለን
እንደ ተራበ እንራባለን
እንደ ተገረፈ እንገረፋለን
እንደ ተቸገረ እንቸገራለን
እንደ ተሰቀለ እንሰቀላለን
እንደ ታመመ እንታመማለን
እንደ ሞተ እንሞታለን
እንደ ተራቆተ እንራቆታለን
እንደ ተነሳ አብረነው እንነሳለን
እንደ ዐረገ እናርጋለን ዘላለም አብረነው እንኖራለን ማለት ነው ።
እንዲህ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ተብለው ይጠራሉ ማለት ነው ። ከክርስቶስ ጋር የታመመ ከክርስቶስ ጋር ይነሳል ። እርሱን መስለውት የሚኖሩ በሁለተናቸው በቃሉ የሚኖሩ በሃይማኖቱ በሕይወቱ ቃሉን የሚሰሙ ቃሉን ሰምተው የሚያደርጉ ። በመስማት አትጸድቁም ብሏል ቅዱስ ጳውሎስ ። ስለዚህ ቃሉን ሰምተው የሚያደርጉ ። ቃሌን እየሰማ በቃሉ ድኛለሁ የሚል ሳይሆን ቃሌን ሰምቶ በቃሌ የሚኖር ቃሉን ሰምቶ የሚያደርግ ሃይማኖቱን የሚያምን የባህርይ አምላክ ነው ብሎ የሚያምን ኹሉም እናምነዋለን ይላሉ የባህርይ አምላክ ነው ትንሳኤ ሕይወት መድኃኒት ሥግው ቃል በተዋሕዶ ብለው የሚያምኑ ። ስለዚህ ሃይማኖቱን የሚያምኑ ቃሉን የሚያደርጉ መንገዱን የሚከተሉ እነዚህ ክርስቲያኖች ይባላሉ ።
ክርስቶስ የተሰቀለው መቼ ነው ?፦ በዕለተ አርብ ። የተነሳውስ ?፦ ዕለተ እሁድ።
ከዕለተ አርብ እና ከዕለተ እሁድ ማንን ትወዳላችሁ !?
አርብ ብትሉ ክርስቲያን አይደላችሁም ። እንዴት ብትሉ ፦ ክርስቲያን የሚባለው ከክርስቶስ ጋር ታሞ ከክርስቶስ ጋር አብሮ የሚነሳ ነው ። አርብን የማትወዷት ከሆነ አብራችሁ መታመም አልፈለጋችሁም ማለት ነው ። ብዙዎቹ በክርስቶስ ስም የተመሰረቱ ድርጅቶች ኹሉ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች ናቸው ። ዕለተ አርብን አይወዱትም ። ክርስቶስ ተነስቷል አድኖኛል እዳ ከፍሎልኛል እንጂ አብረውት ሕማሙን መሳተፍ አይችሉም ። መስቀሉን መሸከም አይወስዱም ። መፆም መጸለይ መስገዱን አይወስዱም ። ለፈቃዳቸው እንጂ ለፈቃዱ መኖር አይወዱም አይፈልጉም ። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ፊልጲስዮስ ፫ ላይ ሲናገር ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል እንቅፋት ሆነው ይመላለሳሉ እያለቀስኩ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው ብሎ ይናገራል ። ስለዚህ አብረውት የታመሙ አብረው ይነሳሉ ።
ሥጋወደሙ በመስቀል ላይ የተፈተተልን መቼ ነው?
ዕለተ አርብ
ዲያቢሎስ በመስቀል የተቀጠቀጠው መቼ ነው?
ዕለተ አርብ
ሲዖል የተበረበረችው መቼ ነው?
ዕለተ አርብ
ገነት የተከፈተው መቼ ነው?
ዕለተ አርብ
የንስሃ በር የተከፈተው መቼ ነው?
ዕለተ አርብ
ነፍሳት ከሲዖል የወጡት መቼ ነው?
ዕለተ አርብ
እና አርብን ምን አድርጋችሁ ነው ምትጠሏት ?፦ አርብን የሚወድ እሁድን ያገኛል ። አብረውት መከራ የሚቀበሉ ክርስቲያኖች ይባላሉ ። አብረው የታመው አብረውት ይነሳሉ ። አብረውት ዝቅ ያሉ ልዑል አምላክ ሲሆን እርሱ ዝቅ እንዳለ መሸሽ እየቻሉ መካድ እየቻሉ ማጭበርበር እየቻሉ በክርስቶስ ስም ዝቅ ያሉት አብረውት ያርጋሉ ። እንግዲህ እኛ ወደ ታች አንወርድም የፈጠረንን ተከትለን እናርጋለን እንጂ !!!
እንግዲህ ወደታች አንወርድም የፈጠረንን ተከትለን ወደ ሰማይ እናርጋለን እንጂ!!!
ከማኅሌት ወደ ዘፋኝነት አትውረዱ!
ከአንድነት ወደ ዘረኝነት አትውረዱ!
ከፆም ወደ ሆዳምነት አትውረዱ!
ስለዚህ በምግባር ወደ ታች ያልወረደ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር አብሮት ያደርጋል ። በዚህ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ተብለው ይጠራሉ ማለት ነው ።
ከአህዛብ የምንለየው የተገለጠው እግዚአብሔር ነው ብለን ስለምናምን ከሎሎቹ
በክርስቶስ ስም ከሚጠሩት ከሌሎቹ ደግሞ የምንለየው በክርስቶስ ፈቃድ ለእራሳችን ሳይሆን ለክርስቶስ ስለምንኖር ነው።
መጨረሻ ላይ በክርስቶስ ስም ስለምንሞት ነው ።
ሮሜ ፲፬፥፰ ላይ ብንሞትም ለክርስቶስ እንሞታለን ብንኖርም ለክርስቶስ እንኖራለን ። በክርስቶስ ስም ተጠምቀው በክርስቶስ ስም ኑረው በክርስቶስ ስም የሚሞቱ #ክርስቲያኖች ተብለው ይጠራሉ።
ለአባታችን ቃለ ሕይወት ቃለ በረከት ያሰማልን በእድሜ በጸጋ ያቆይልን።
የተማርነውን በልቡናችን ያሳድርልን።
ጸሐፊ ራሔል የተዋሕዶ ተማሪ @felgehaggnew @felgehaggnew