Get Mystery Box with random crypto!

ከለላ ለሚሹ ሴቶች ድምጽ ለመሆን በማለም የተቋቋሙ ማህበራት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ተገ | AHADU RADIO FM 94.3

ከለላ ለሚሹ ሴቶች ድምጽ ለመሆን በማለም የተቋቋሙ ማህበራት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ በየጊዜው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ፍትህ እንዲያገኙ ለማስቻልና ለእነዚሁ ሴቶች ድምጽ ለመሆን ባለመ መልኩ የተቋቋሙ የሴት ማህበራት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ እንዳልሆነ አሃዱ ያነጋገራቸው የሲቪል ማህበራት ገልጸዋል፡፡
የቪ-ኮድ ኢትዮጵያ መስራችና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ጥምረት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ታደለ ደርሰህ ባለፉት አመታት በሃገሪቱ የተከሰቱትን ግጭቶች እንዲሁም የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በርካታ ሴቶች የጾታዊ ሆነ ስነ ልቦናዊ ጥቃት ሰለባ ቢሆኑም በርካታ የሴት ማህበራት ግን ዝምታን በመምረጥ አፈግፍገዋል ብለዋል፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ የሰላም አየር ሲነፍስ ጠብቀው ብቅ ብቅ የሚሉ የሴት ማህበራት በስፋት ተስተውለዋል ያሉት አቶ ታደለ ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለዉና የተቋቋሙበትን አላማ የሳተ ነው ሲሉም ተችተውታል፡፡
ሌላኛው አሃዱ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘየደ ገብረጻዲቅ በበኩላቸው የአቶ ታደለን ሃሳብ በመጋራት ለሴቶች ከለላ ከመስጠት አኳያ አለማቀፍ ህጎች እንዲከበሩ ከመስራት ይልቅ ከአላማቸው በሚቃረኑ ተግባራት ላይ ተሳታፊ ሆነው መገኘታቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በማህበራቱ በኩል እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ምን እየሰራችሁ ትገኛላችሁ ሲል አሃዱ ያነጋገራቸው የኢትዮጲያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላም ሃላፊነታቸውን የማይወጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የክዋኔ ሪፖርትን ጨምሮ የተለያዩ ክትትሎችን በማድረግ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ማገድ ድረስ የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

የግጭትና ጦርነት ቀጠና ሆነው በቆዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የጾታዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸው አሳሳቢ ሆኖ ቢቆይም አብዛኛዎቹ ለሴት ብለዉ የተቋቋሙ ማህበራት በሌሎች ስራዎች ከመደመጣቸዉ በላይ ስለ ጉዳዩ ምንም ሳይሉ ዝምታን መምረጣቸዉ ይታወቃል፡፡

አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ድህረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ፌስቡክ:https://www.facebook.com/ahaduradio
ትዊተር፦https://twitter.com/ahadu_radio?lang=en
አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን #አሐዱ_24