Get Mystery Box with random crypto!

ፍሉሃ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ ቃል የገባልንን ምትክ ቤት ሳይሰጠን ከቦታዉ | AHADU RADIO FM 94.3

ፍሉሃ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ ቃል የገባልንን ምትክ ቤት ሳይሰጠን ከቦታዉ እንድንነሳ በህግ አካላት እየተገደድን ነዉ ሲሉ ቅሬታቸዉን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የቀበሌ ቤትና ህጋዊ የግል ይዞታ ለነበራቸው በፍልውሃ አካባቢ ለነበሩ የልማት ተነሺዎች በሙሉ ቃል የተገባላቸውን መኖሪያ ቤት አስረክቤያለሁ ሲል አስታውቋል፡፡ በፍልውሃ አካባቢ ኑሯቸውን በሸራ መጠለያ ውስጥ ያደረጉ የልማት ተነሺዎች ቃል የተገባልን የመኖሪያ ቤት ድጋፍ አልተፈጸመልንም ብለው ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ለረጅም አመታት በሸራ መጠለያ ውስጥ ኑሯችንን ስንመራ ነበር ነገር ግን ምንም አይነት ምትክ ቦታ ሳይሰጠን በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ ከቦታዉ ላይ እንድንነሳ ተገደናል ሲሉ ለአሃዱ እንዲህ ቅሬታቸዉን አሰምተዋል፡፡ አሃዱም በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ፕሬስ ሴክሬተሪ አቶ በረከት ታከለን አነጋግሯል፡፡አቶ በረከት በምላሻቸውም በፍልውሃ አካባቢ የሚገኙ የግል ይዞታ መሬት ለነበራቸው የልማት ተነሺዎች 1.1 ቢሊየን ብር ካሳ መከፈሉንና 5.6 ሄክታር ተለዋጭ መሬት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በቀበሌ ቤት ይኖሩ ለነበሩ ከ400 በላይ ዜጎች ደግሞ ተለዋጭ የቀበሌ ቤት አስረክበናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቀበሌ ቤት ወይም የግል ይዞታ ለነበራቸው ዜጎች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ምላሽ መሰጠቱን ገልጸው አሁን እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎች ግን የቀበሌ ቤት ሳይኖራቸው ሸራ ወጥረው ኑሯቸውን ይመሩ በነበሩ ዜጎች ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ለእነዚህ ዜጎች በከተማ አስተዳደሩ የተዘጋጀ ምንም አይነት ተለዋጭ ቤት እንደሌለም አክለው ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቦታዉ ላይ ተጠልለዉ ሲኖሩ 30 እና 40 አመታት እንዳለፋቸዉ ገልጸዉ ካለባቸዉ የኑሮ ጫና እና የቤተሰብ ቁጥር አኳያ የትኛዉን ቤት ተከራይተዉ ለመኖር አቅም እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ አካባቢዉ ለፈርስ ሲል የከተማ አስተዳደሩ የደሃ ደሃ ቤት ለእናንተም ይሰጣችኃል ብሏቸው እንደነበር ጠቅሰዉ አሁን ይህ ቃል የተገባዉ ነገር ለአንዳንድ ሰዎች ተመርጦ ሲሰጥ ተመልክተናል ሲሉ ጣቢያችን ድረስ በአካል መጥተዉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ቀበሌ ቤት ወይም የግል ይዞታ ኖሯቸው ምንም አይነት ተለዋጭ ቦታ አላገኘንም ብለው ቅሬታ ለሚያነሱ የልማት ተነሺዎች ግን ቅሬታቸውን ለማስተናገድ ዝግጁ ነዉ ሲሉ አቶ በረከት ተናግረዋል፡፡

አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
ድህረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ፌስቡክ:https://www.facebook.com/ahaduradio
ትዊተር፦https://twitter.com/ahadu_radio?lang=en
አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን #አሐዱ_24