Get Mystery Box with random crypto!

የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የባጃጅ ተሸከርካሪዎቻቸዉ በጸጥታ አካላት እንደተወሰዱና እስካሁን | AHADU RADIO FM 94.3

የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የባጃጅ ተሸከርካሪዎቻቸዉ በጸጥታ አካላት እንደተወሰዱና እስካሁን እንዳልተመለሱላቸዉ አሽከርካሪዎች ለአሃዱ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊሰ ኮምሽን በበኩሉ በህገ ወጥ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን እና 194 የባጃጅ ተሽከርካሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጻል፡፡
ለአሃዱ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የባጃጅ አሽከርካሪዎች እንደተናገሩት ስራ ከማቆማቸው ባሻገር ባጃጆቻቸው ተጭኖ በመወሰዱ የት እናዳለ እንደማያውቁ እና በርካታ የስራ ባልደረቦቻቸው በአሁኑ ሰአት በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጸው የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ በበኩላቸው በከተማው ላይ የጸጥታ ችግር እንዲፈጠር ከማድረግ ባሻገር በአካባቢው የትራፊክ መጨናነቅ እንዲኖር ያደረጉ እና የጸጥታ አካላት ላይ ጥቃት የፈጸሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን ጠቅሰዉ ከጸጥታ ችግሩ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የነበራቸውን 194 ገደማ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉና አስፈላጊው የህግ ሂደት እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ለአሃዱ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ኮማንደር ማርቆስ አክለውም በተለይ ከጸጥታ አካላት ጋር ግጭት የፈጠሩ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸው ጉዳያቸው በህግ አግባብ እየተጣራ እንደሚገኝም አስታዉቀዋል፡፡
ማንኛውም የመብት ጥያቄ በህግ አግባብ መሰረት መጠየቅ አለበት ያሉት ምክትል ኮማንደሩ ከዛ ውጪ የሆነ ነገር በህግ እንደሚያስጠይቅ ማህበረሰቡ ሊገነዘብ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡ በአዲስ አበአባ ከተማ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ካሳለፍነዉ ሳምንት ጀምሮ እንዲቋረጥ መደረጉ የሚታወቅ ነዉ፡፡