Get Mystery Box with random crypto!

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያለፍርድ የታሰሩ ሰዎች እንግልትና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን | AHADU RADIO FM 94.3

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ያለፍርድ የታሰሩ ሰዎች እንግልትና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አስታዉቋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው የሰላምና ፀጥታ ችግር ምክንያት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳደር የፈረሰ መሆኑን እና ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደ አዲስ የዞን አስተዳደር ቢቋቋምም በአካባቢው የፍርድ ቤትና አቃቢ ሕግ ቢሮዎች ተቋቁመው ሥራ ባለመጀመራቸው የአካባቢው ሰዎች ያለአግባብ እስር እየተፈጸመባቸው መሆኑን ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡
መንግሥት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በፍርድ ቤትና ዓቃቤ ሕግ ዕጦት ምክንያት እየተጣሰ ያለውን ፍትሕ የማግኘት መብትና እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያስቆም ጠይቋል፡፡
ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ያለምንም ከሳሽ በፖሊስ ጣቢያ እንግልትና ድብደባ እየደረሰባቸው ለረዥም ጊዜ ማለትም ከሁለት እስከ ዘጠኝ ወራት ታስረው እንደሚገኙ ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ መቻሉን ገልጻል፡፡
የሰዎችን ፍትህ የማግኘት መብት ለማስጠበቅ የፍትህ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት ባለመቻላቸው ያለ ከሳሽ በፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ሰዎች እንግልትና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን አመላክቷል፡፡
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚመለከተው የፍትሕ አካል በፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅ ትዕዛዝ የተላለፈላቸዉን እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈታና ለረዥም ወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ታስረው የሚገኙትን ሰዎች ፍርድ ቤት በማቅረብ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን እንዲያስጠብቅ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ጠይቋል፡፡