Get Mystery Box with random crypto!

ስለ ጦርነቱ- በጥቂቱ ------- አፈንዲ ሙተቂ ------- 'ስለሙዚቃ መጻፍ አበዛህ። ስለጦርነቱ | AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴

ስለ ጦርነቱ- በጥቂቱ
-------
አፈንዲ ሙተቂ
-------
"ስለሙዚቃ መጻፍ አበዛህ። ስለጦርነቱ ተናገር እንጂ?!" የሚሉ ድምጾች በዝተውብኛል። በመጀመሪያ እንዲህ ዓይነት መመሪያ መሰል ጥያቄ እንደማልቀበል የገለጽኩትን መድገም እፈልጋለሁ። የምጽፍበትን አጀንዳ የምወስነው እኔ ብቻ ነኝ። ይህንን ያዙልኝ።
------
ጦርነቱን በተመለከተ ያለኝ አቋም አልተቀየረም። አይቀየርምም።

ጦርነት ለምንም ነገር መፍትሔ ሆኖ አያውቅም። ጦርነት አለመግባባቶችን ያባብሳል እንጂ የመፍትሔ ሐሳብ አያመነጭም። ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም። ጦርነት በብዙ ዓመታት ልፋት የተሰራውንና የተገነባውን የሀገር ሀብትና የግለሰቦች ይዞታ ከማጥፋት በቀር ምንም ፋይዳ የለውም።

አዎን! ይህንን አስረግጬ እናገራለሁ። ጦርነት መሰረተ ልማቶችን የሚያወድም፣ ሱቆችንና የገበያ አዳራሾችን የሚፈነቃቅል፣ አዝመራን የሚያቃጥል፣ የብዙዎችን ነፍስ የሚቀጥፍ፣ ብዙዎችን የሚያፈናቅል፣ ቤተሰብን የሚበትን፣ ህጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋዊያንን ለዋይታና ለሰቆቃ የሚዳርግ፣ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀውስ መንስኤ የሚሆን፣ ሀገሮችንና ከተሞችን የሚያፈራርስ የጥፋት መንገድ ነው።

ጦርነትን ተገደው ይገቡበት ይሆናል። ፍትሐዊነት ሲጠፋ ጦርነት ማወጅ ያለ ነው። ለምሳሌ ሀገር በውጪ ሃይል ብትወረር ጦርነትን ማወጅ ግዴታ ሊሆን ይችላል። ታዲያ በእንዲያ ዓይነት ጊዜም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላማዊ አማራጮች ነው። ሁሉም የሰላም በር ዝግ ሲሆን ወደ ጦርነት መግባቱ ነው ፍትሓዊ መፍትሔ የሚያስገኘው። ሰላማዊ አማራጮች ሳይሞከሩ ወደ ጦርነት መግባት ራስን እንደማጥፋት ይቆጠራል።

እጅግ አስቀያሚው ጦርነት ደግሞ በአንድ ሀገር ዜጎች መካከል የሚካሄደው ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጦርነት ከቁሳዊና ሰብዓዊ ውድመቱ ባሻገር በረጅም ታሪካዊ ሂደት የተገነባውን የህዝቦችን ብሄራዊ መስተጋብር የሚያናጋ እና ሀገር እንድትበተን መንስኤ ሊሆን የሚችል ክፉ ደዌ ነው።
------
አምና እንደዚህ እያልኩ ስጽፍ ነበር። አሁንም አቋሜ ይኸው ነው። ዛሬም ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን አቁመው ችግራቸውን በውይይትና በድርድር ብቻ ይፍቱት እላለሁ። ሰላም!!
-----
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 22/2014