Get Mystery Box with random crypto!

የወጋየሁ ደግነቱ “አርኬ ሁማ” እና “ወረት” ----- ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ ----- በድፍን ኢት | AfandishaHarar 🇪🇷🇪🇹🇯🇴🇸🇩🇪🇭🇸🇴

የወጋየሁ ደግነቱ “አርኬ ሁማ” እና “ወረት”
-----
ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ
-----
በድፍን ኢትዮጵያ ከሚታወቁት የአፋን ኦሮሞ ዘፈኖች አንዱ “አርኬ ሁማ” ይሰኛል። ዘፋኙ ሟቹ ድምጻዊ ሻለቃ ወጋየሁ ደግነቱ ነው። ይህ ዘፈን በዜማና ግጥም አሰካኩም ሆነ በሚያስተላልፈው መልዕክት “ዘመን አይሽሬ” ከሚባሉት አንዱ ነው። የዚህ ዘፈን አዝማች የህዝብ ነው። የሀረርጌ ኦሮሞ ወጣቶች ከጥንት ጀምሮ ሲቀባበሉት ነው የኖሩት። ዜማውን ከህዝቡ ወደ መድረክ አምጥቶ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሰማው ያደረገው ሰው ደግሞ “አቡበከር ሙሳ” ይባላል። አቡበከር “አርኬ ሁማ”ን እንደ አዝማች በማድረግ የዘፈኑን ግጥም ውብ በሆነ የቃላት ቅንብር ጽፎታል። በመሆኑም በአዝማቹ ግጥም በመሀል መንገድ ላይ ተንጠልጥሎ የቀረው የዘፈኑ መልዕክት በአቡበከር ሙሳ ውብ ብዕር የተሟላ ሆኗል።

“አርኬ ሁማ ሁማ አርኬ ሁማ (Arke humaa humaa arkee humaa)
ኤጋ ሆሪ ታቴ ጃለልቲ ነማ (Eega horii taate jaalalti namaa)
ረብቢ መሌ ነምኒ ኒጂጂረማ” (Rabbi malee namni nijijjirama)

ይህ የግጥሙ አዝማች ነው። በአማርኛ እንደሚከተለው ሊተረጎም ይችላል።

“አየሁት ግድየለም አየሁት ግድየለም”
“የሰው ልጅ መውደድ ከሆነ ለገንዘብ
“ፈጣሪ እንጂ ሰውስ ይቀየራል ግድየለም”

አቡበከር በዚህ ላይ ነው የሚከተሉትን መስመሮች የጨመረው።

“አርኬ ሁንዳ ሁንዳ አርኬ ሁንዳ (Arke hunda hunda arge hunda)
አርኬ ሁማ ሁማ አርኬ ሁማ (Arke humaa humaa arge humaa)
አምማ ሆሪ ዸብናን ከን ነ ዴይሱ ማሉማ (Amma horii dhabnaan kan nadheeysu maaluma)
አርኬ ሁማ (Arke humaa)
----------
አዱኛፍ ጂርተኒ አኺራፍ ቴይሳኒ (Adunyaaf jirtanii akhiraaf teysanii
ዋን ኢሲን ኤግገተን ኢሲን ዋ ሂንቤይተኒ (Waan issin eeggatan isin wa hinbeetanii)
አርኬ ሁማ (Arke humaa)
----------
ሀማሬሲ ሂንጨቡ ኑመ ሚጪረማ (Hammarreessi hincabu numa micciiramaa
ገራን ኢልማ ነማ ቶርባ ጂጂረማ (Garaan ilma namaa torba jijjiramaa)
አርኬ ሁማ (Arke humaa)
------------
ግጥሙ ወደ አማርኛ ሲተረጎም እንደሚከተለው ይሆናል (ተርጓሚው መኮንን ታደሰ መኮንን ነው)።

ሁሉን አየሁታ… ሁሉን አየሁታ…
ንዋይ ብቻ ሲሆን የሰው ልጅ ውለታ፣
ሁሉም ይቀየራል ያለርሱ ያለጌታ።
--------
አየሁት ሁሉንም አየሁት ሁሉንም፣
አየሁት ግድየለም አየሁት ግድየለም
አሁን ሀብት ባጣ…
መሸሽን ምን አመጣ?
------
ለአዱኛ ስትሮጡ ለንዋይ ስትኖሩ
ምን እንደሚገጥማችሁ…
ምን እንደምትሆኑ…
አይታወቅ ዳሩ!!
--------
ዝግባ አይሰበር ይጠማዘዝ እንጅ
አስሬ ይቀየራል አመሉ የሰው ልጅ።
------
ግጥሙ ስለ"ወረት" ነው የሚያወሳው።
አዎን! የሰው ልጅ ወረተኛ ነው። “አይደለሁም” ቢል እንኳ ወረተኛነት ሁልጊዜም ይፈታተነዋል። ማግኘትና ማጣት የዚህች ዓለም ነጸብራቅ በመሆናቸው ማንንም ሊያጠቁ ይችላሉ። ወረተኛነት ግን ሁሉም ዘንድ ላይደርስ ይችላል። ሰዎች ሽንጣቸውን ገትረው ከታገሉት “ወረት”ን በሩቁ ማስቀረት ይችላሉ። አለመታደል ሆኖ አብዛኛው ሰው ለወረት ይንበረከካል። “ፈረንካ” ሲቋጥር መቶ ሰማኒያ ዲግሪ ያህል ይቀየራል። ትላንት አብሯቸው ኳስ ሲጫወትና ማዕድ ሲቋደስ የነበሩትን ሰዎች በቆረጣ እያየ “እእ…ማን ነህ አንተ?..ስምህ ጠፋብኝ.. ወዘተ…” ማለት ይጀምራል። ዘመዶቹ ሊግጡት ያቆበቆቡ በቅሎዎች ይመስሉትና በሩቁ ይሸሻቸዋል። የባሰበት ደግሞ አፍ የፈታበትን ቋንቋ፣ የተወለደበትን ቀዬ እና ሀገሩን ጭምር እስከ መካድ ይደርሳል።

ታዲያ የሚያሳዝነው ነገር በ“ፈረንካ” ልቡን እያማለለ የቀየረው የ“ወረት” ልክፍት ነገን ጭምር የሚያስረሳው መሆኑ ነው። ነገ ሞት እስትንፋሱን ቀጥ አድርጎ ሊያቆመው ቢመጣበት “ወረት” ሊያድነው ነውን? ከሞት በኋላ ባለው ህይወት ከሚመጣበት ቅጣትስ “ወረት”ን አስጥለኝ ብሎ ሊማጸነው ነውን? አረ ምናለ.. በፈረንካ ባንታወር!… አረ ምናለ በወረት ባንታለል!…… (የራሴን ፍልስፍና ጨማመርኩበት አይደል? በርግጥ በግጥሙ ውስጥ ይህ ሁሉ የለም። መልዕክቱ ግን ከዚህም በላይ ነው… ብዙ ብዙ ያስጽፋል….)
------
እንግዲህ “ወረት”ን አላህ ይያዝልን። ወረተኞችም አደብ ግዙልን። ጌታችን የሰጠን ይበቃናልና በፍቅር አብረን እንኑር። ለሁሉም ይህንን የዩ-ቲዩብ ቪዲዮ ክፈቱና ወጋየሁ ደግነቱን ስሙት። የልጅነታችንን ዘመን እያስታወስን “ወረት”ን በጋራ ወግድ እንበለው።

አርኬ ሁማ አርኬ ሁማ…
ኤጋ ሆሪ ታቴ ጃለልቲ ነማ…
ረብቢ መሌ ነምኒ ኒጂጂረማ
አርኬ ሁማ!...




------
አፈንዲ ሙተቂ
ነሐሴ 28/2014