Get Mystery Box with random crypto!

1፤ በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች ማክሰኞ'ለት በትንሹ 55 ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋ | አድስ ዜና

1፤ በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች ማክሰኞ'ለት በትንሹ 55 ሰላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ሲሉ የዓይን ምስክሮች መናገራቸውን ጠቅሶ ዶይቸቨለ ዘግቧል። ታጣቂዎች ጥቃቱን ፈጸሙ የተባለው በዞኑ ኡሙሩ ወረዳ፣ አገምሳ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ነው። ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ግድያውን የፈጸሙት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ከከተማዋ ዕሁድ'ለት መነሳታቸውን ተከትሎ ነው ሲሉ እማኞች ተናግረዋል። ነዋሪዎች ተፈጸመ ስላሉት ግድያ የአስተዳደር እና ጸጥታ ኃላፊዎች ያሉት ነገር የለም።

2፤ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በሰሜን ኢትዮጵያ በመንግሥት እና በሕወሃት መካከል ያገረሸው ጦርነት ለመምህራን ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት እንቅፋት እንደፈጠረበት ትናንት በሰጠው መግለጫ መናገሩን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። መምህራንና ተማሪዎች በጦርነቱ መፈናቀላቸውንና ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን የጠቀሰው ማኅበሩ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሰላም ንግግር እንዲጀምር ጠይቋል። ለትግራይ ዕርዳታ ፈላጊዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ እንዲቀጥልም ማኅበሩ ጥሪ አድርጓል።

3፤ የኢትዮጵያ መርከብ እና ሎጅስቲክስ ድርጅት በሰኔ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3.6 ሚሊዮን ካርጎ በማጓጓዝ 3 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አስኪያጅ ማሞ ምኅረቱ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። የድርጅቱ ትርፍ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ121 በመቶ ብልጫ እንዳለው ማሞ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያገኘው ትርፍ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ90 በመቶ እድገት እንዳለው ማሞ ጠቁመዋል።

4፤ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ራማፎዛ በአገራቸው በውጭ ዜጎች ላይ የተቃጣውን ተቃውሞ መንግሥታቸው እንደማይታገስ ለፓርላማው መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል። በፕሪቶሪያ "ዳዱላ" የተባለ በውጭ ፍልሰተኞች ላይ ያነጣጠረ አዲስ ንቅናቄ፣ ፍልሰተኞች እና የውጭ ዜጎች ሕክምና እንዳያገኙ ማገድ መጀመሩን መንግሥት ገልጧል። ንቅናቄው ዜጎች በሆስፒታሎች ለሚጠብቁት ረጅም ወረፋና ጥራት የለው ላሉት የሕክምና አገልግሎት ፍልሰተኞችን ተጠያቂ ያደርጋል። በአገሪቱ አራት ሚሊዮን የውጭ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።