Get Mystery Box with random crypto!

አጫጭር ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥት እና ሕወሃት ግጭት አቁመው የሰላ | አድስ ዜና

አጫጭር ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥት እና ሕወሃት ግጭት አቁመው የሰላም ንግግር እንዲጀምሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጥሪ አድርጓል። ኮሚሽኑ አፍሪካ ኅብረት፣ ተመድ፣ ሲቪክና የሐይማኖት ተቋማትና መገናኛ ብዙኀን ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆም፣ ንግግር እንዲጀመርና በጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ክልሎች የሰላማዊ ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቋል። ኮሚሽኑ ሁሉም ወገኖች የግጭቱ ተጎጅ የሆኑ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት፣ ደኅንነት፣ አካላዊ እና ሞራላዊ ሁኔታ እና የሰውነት ክብር እንዲያከብሩ ተማጽኗል።

2፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተመድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን መንግሥት እና ሕወሃት አዲስ ያገረሸውን ግጭት ባስቸኳይ አቁመው ንግግር እንዲጀምሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ኮሚሽኑ ረድዔት ድርጅቶች ለትግራይ የሚያቀርቡት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀጥል መንግሥትና ሕወሃት ጥረት እንዲያደርጉ ተማጽኗል። በቅርቡ በመቀሌ በሙዓለ ሕጻናት ማዕከል ላይ ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ስለመጎዳታቸው የወጡ ሪፖርቶችና ሰሞኑን በአማራ ክልል ቆቦ ከተማ በተካሄደ ማጥቃት ላማዊ ሰዎች ዒላማ ሆነዋል መባሉ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጧል።

3፤ ትናንት ለይፋዊ ሥራ ጉብኝት አልጀሪያ የገቡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱልመጂድ ታቡኔ ጋር መወያየታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአልጀሪያው ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ዙሪያ መነጋገራቸውን ገልጸዋል። ዐቢይ ኢትዮጵያ እና አልጀሪያ ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ የሚችሉባቸው በርካታ ዘርፎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

4፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኀንና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በሕግ ተጠያቂ አደርጋለሁ በማለት ማስጠንቀቁን ኢዜአ ዘግቧል። መገናኛ ብዙኀን በጦርነት ጊዜ ለአገሪቱ ብሄራዊ ጥቅሞ፣ ለሰላምና ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ያሳሰቡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ፣ "ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ግብዓት የሚውሉ መረጃዎችን" ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚያስፈልግም መክረዋል።

5፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ የሙከራ አገልግሎቱን መጀመሩን በድረገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። የሙከራ አገልግሎቱ ደንበኞች በሚገዟቸው የኩባንያው የስልክ ሲም ካርዶች የድምጽ፣ የጽሁፍና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን መስጠት ነው። ኩባንያው አንድን የሳፋሪኮም የሞባይል ስልክ ሲም ካርድ የሚሸጠው በ30 ብር ነው።

6፤ በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ አፍሪኮም ዋና አዛዥ ጀኔራል ማይክል ላንግሌይ ዛሬ ሞቃዲሾ መግባታቸውን በሞቃዲሾ የአሜሪካ ኢምባሲ በትዊተር ገጹ አስታውቋል። ጀኔራል ላንግሌይ ነውጠኛውን አልሸባብ በጋራ መዋጋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከሱማሊያው መከላከያ ሚንስትር አብዱልቃድር ሞሐመድ ኑር ጋር መነጋገራቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ጀኔራል ላንግሌይ የአፍሪኮም አዲሱ ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙት በወሩ መጀመሪያ ነበር።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ4344 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ4831 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 59 ብር ከ2586 ሳንቲም፣ መሸጫው 60 ብር ከ4438 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ52 ብር ከ5078 ሳንቲም ሲገዛ እና በ53 ብር ከ5580 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል