Get Mystery Box with random crypto!

'ተያይዘን ኢትዮጵያ' ታዳጊዎችን በስብዕና የማነጽ ተግባሩን አገር አቀፍ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ | Addis Maleda - አዲስ ማለዳ

"ተያይዘን ኢትዮጵያ" ታዳጊዎችን በስብዕና የማነጽ ተግባሩን አገር አቀፍ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ

ከነሐሴ 27 ጀምሮ በአዳማ ከተማ የከተማዋ ወላጆችና ተማሪዎች የሚገናኙበት ፌስቲቫል መዘጋጀቱም ተገልጿል


አርብ ነሐሴ 20 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) "ተያይዘን ኢትዮጵያ" በጎ አድራጎት ድርጅት "የሚሰጥ ዘር" በሚል መሪ ቃል ታዳጊዎችን በስብዕና የማነጽ ተግባሩን አገር አቀፍ ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል።

ድርጅቱ በአዳማ ከተማ ከነሐሴ 27 ቀን 2014 ጀምሮ በአዳማ ከተማ ወላጆችና ተማሪዎች የሚገናኙበት ፌስቲቫል ማዘጋጀቱንም ገልጿል፡፡

ከዓመት በኋላ ታዳጊ የማነጹን በጎ ተግባር አገር አቀፍ ለማድረግ መታቀዱንና በአደማ ከተማ ፌስቲቫል መዘጋጀቱን የድርጅቱ መስራችና ዳይሬክተር ምስጋናው ታደሰ በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብስረዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዓላማ ጦርነት፣ መጨካከን እንዲሁም አለመተጋገዝ እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት ታዳጊዎችን በመታደግ የመፈቃቀርና የመተሳሰብ ባህላቸው እንዲጠነክር ማድረግ ነው ተብሏል፡፡

ድርጅቱ በአዳማ ከተማ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ለአንድ ዓመት ታዳጊዎችን በሥነ ምግባር የማነጽ በጎ አድራጎቱን እንዳከናወ የተናገሩት ምስጋናው፤ እስከ ጳጉሜ ስድስት ይቆያል በተባለው ፌስቲቫል ወላጆችና ተማሪዎች በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል፤ በፌስቲፋሉ ተሳታፊ የሚሆኑ ሰዎች አንድ ደብተር ወይም እስክርቢቶ ለፌስቲቫሉ እንደ መግቢያ አድርገው እንዲያበረክቱና በዚህም የትምህርት ቁሳቁሶችን ለመግዛት ለሚቸገሩ ተማሪዎች ወጭ ለመሸፈን መታቀዱ ተመላክቷል፡፡

በዚህ "የሚሰጥ ምርት ዘር" በሚል ትውልድን የማነጽ ሥራ አንድ ተማሪ በዓመት ውስጥ 32 ጓደኛ አፍርቶ የሚወጣበት አጋጣሚ ስለመኖሩም ተጠቅሷል፡፡

ድርጅቱ “ራዕይህ የአንድ ዓመት ከሆነ ስንዴ ዝራ፤ ራዕይህ የ10 ዓመት ከሆነ ዛፍ ትከል፤ ራዕይህ የሕይወት ዘመን ከሆነ ትውልድ አንጽ” በሚል መፈክር ታዳጊን ለማነጽ እየሰራ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

የሚፈለገውን ያህል ህጻናቱን ለማነጽ ቢያንስ 10 ዓመት ያስፈልጋል ያሉት ምስጋናው፤ ራዕዩ ግን ትውልድን ማነጽና ዘላለማዊ ነው ብለዋል፡፡

በፌስቲቫሉ ቢያንስ 30 ሺሕ ተሳታፊ ይገኛል ተብሎ እንደሚታሰብ እና እስካሁን 230 በላይ ሰዎች በፕሮግራሙ እንደሚሳተፉ ማስታወቃቸውን ምስጋናው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢዮብ ትኩዬ
________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n