Get Mystery Box with random crypto!

ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ የተፈፀመውን የዶግማ፣ የቀኖና እና አስተዳደራዊ ጥሰት አስመልክቶ ተወያይቶ | አዲስ ሪፖርተር - NEWS

ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ የተፈፀመውን የዶግማ፣ የቀኖና እና አስተዳደራዊ ጥሰት አስመልክቶ ተወያይቶ ተገቢውን ለመወሰን ለሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪ አስተላለፈ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
  1. በክልል ትግራይ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በክልሉ ከሚገኙት አህጉረ ስብከት ጋር ተቋርጦ የነበረውን መዋቅራዊ ግንኙነት ችግር በውይይት እንዲፈታ ቅዱስ ሲኖዶስ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና ልዑካኑን በአካል ልኮ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ተብለው በሚጠሩበት በማዕከላዊ ትግራይ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሐምሌ 15 እና 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በተከናወነ ሕገ ወጥ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት መፈጸሙን በመገናኛ ብዙኃን ለማወቅ ችለናል፡፡ በመሆኑም በዚህ የዶግማና የቀኖና ጥሰት ተግባር የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በእጅጉ አዝኗል፡፡ 

2. በመሆኑም የተከሰተው የዶግማ፣ የቀኖና እና አስተዳደራዊ ጥሰት አስመልክቶ ተወያይቶ ተገቢውን ለመወሰን ለሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪ ተላልፏል፡፡

3. የስብሰባው ቀን ሊራዘም የቻለው በውጭው ክፍለ ዓለማት ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት መገኘት ስላለባቸው የጉዞ ቀኑ እንዳያጥር እና በሀገር ውስጥ የሚገኙትም ሊቃነ ጳጳሳት ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል ምክንያት ለአገልግሎት ወደ አህጉረ ስብከታቸው የሄዱ በመሆኑ ለመመለሻ የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

4. በየደረጃ ያሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሥራ ኃላፊዎች እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምዕመናን ከአሁን ቀደም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በደረሰው ፈተና በሐዘንና በጸሎት ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን በመቆም ላሳያችሁት ጽናት እያመሰገንን አሁንም በደረሰው ፈተና እንዳሁን ቀደሙ ሁሉ በሐዘንና በጸሎት ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን ጸንታችሁ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

5. በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ተገቢውን ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በትግዕስት እንድትጠብቁ እናሳስባለን፡፡

6. ምንም እንኳን ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ ጥሪው በደብዳቤ የተላለፈ ቢሆንም የመልእክቱ በፍጥነት መድረስ ካለው ስጋት አንጻር የችግሩን ተደጋጋሚነትና አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ክፍለ ዓለማት የምትገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ተጠቃላችሁ ወደ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ እንድትመጡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡

7. ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ሚዲያዎችና ሌሎች መገናኛ ብዙኃን ይህን መልዕክት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን መልእክቱን በማስተላለፍ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ በቤተ ክርስቲያናችን ስም እንጠይቃለን፡፡

@Addis_Reporter
@Addis_Reporter