Get Mystery Box with random crypto!

'መንግስት ስልጣን የሰጣቸው የአብን አመራሮች ፓርቲው የተመሰረተበትን ዓላማ በመተው የመንግስት ጉዳ | አዲስ ነገር መረጃ

"መንግስት ስልጣን የሰጣቸው የአብን አመራሮች ፓርቲው የተመሰረተበትን ዓላማ በመተው የመንግስት ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነዋል" - የአብን ጽ/ቤት ሃላፊ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የጽህፈት ቤት ሃላፊ ቴዎድሮስ ሀይለማርያም (ዶ/ር) "መንግስት ስልጣን የሰጣቸው የአብን አመራሮች ፓርቲው የተመሰረተበትን ዓላማ በመተው የመንግስት ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነዋል" ሲሉ ለአሻም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል መንግስትና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል እየተደረጉ ያሉ ግንኙነቶችን አስመልክቶ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አመራሮች ለሁለት መከፈላቸውን ሃላፊው ይፋ አድርገዋል።

ሀላፊው እንደሚሉት የሁለቱ አካላት ግንኙነት ሰላም እስካመጣ ድረስ መልካም ነው የሚሉ አመራሮች አሉ በአንፃሩ  ደግሞ ተጠያቂነት ሳይኖር ጦርነቱን በበላይነት ሲመሩ የነበሩ አካላት የሚያደርጉት ውይይት አግባብ አይደለም የሚሉ መኖራቸውን ነግረውናል፡፡

እንደ እርሳቸው አገላለፅ "ይህ መከፋፈል የመጣውም በመንግስት ሹመት ተደልለው የመንግስት ስራ አስፈፃሚ የሆኑ የንቅናቄው አመራሮች በመኖራቸው ነው፡፡" ሲሉ ተችተዋል።

ግማሹ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ በመንግስት ካቢኔ ውስጥ ተቀምጠው የአማራ ህዝብን ሳይሆን የገዢውን ብልፅግና ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነዋል የሚሉት ቴዎድሮስ "በአማራ ህዝብ ላይ ይህ ሁሉ በደል ሲፈፀምበት ንቅናቄው ከተመሰረተበት ዓላማ ውጭ የመንግስትን ጉዳይ በማስፈፀም የአማራ ህዝብን የሚታገል ድርጅት ሆኗል" ሲሉም አክለዋል።

ሃላፊው  መፍትሔ ብለው በማስቀመጡት ሃሳብም "አብን ይህን ጉዳይ አስታርቆ  ሊቀጥል የሚችለው በመንግስት ስልጣን ውስጥ ያሉ ሰዎች ከስልጣናቸው ሲለቁ አልያም ፓርቲውን መልቀቅ ሲችሉ ብቻ ነው" ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ሀላፊው አክለውም "ለአማራ ህዝብ እታገላለሁ እያሉ ለሕዝቡ ጠላት የሆነው መንግስትም አካል ነኝ ማለት ሊሆን አይችልም፤ ምን አልባትም ድርጅቱ ጉባኤውን ካካሄደ እነዚህን ሰዎች ምርጫቸውን ይሰጣቸዋል" ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

Via Asham

@Addis_News
@Addis_News