Get Mystery Box with random crypto!

በጉጂ ዞን በኦሮሞ እና በሲዳማ ብሔር ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት | አዲስ ነገር መረጃ

በጉጂ ዞን በኦሮሞ እና በሲዳማ ብሔር ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደረሰ

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በሲዳማ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተፈጠረ ግጭት ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱ ተገለጸ፡፡

በኹለቱ ብሔር ተወላጆች መካከል የቆየ የድንበር ይገባኛል ክርክር መኖሩን እና ይህንም ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት ግጭት እና አለመግባባት እንደሚፈጠር በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡

ለአብነትም ሐሙስ ሰኔ 01/2015 ግጭት ተፈጥሮ በኹለቱም ብሔር ተወላጆች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት መደረሱን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

አክለውም፤ በሲዳማ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተለይም ጌዴኦ፣ ከማኒ፣ ገደብ እና ገርበማ በተሰኙ ሥፍራዎች በተደጋጋሚ ግጭት እንደሚከሰት እና በዚህ ሳቢያም ከኹለቱም ወገን ሰዎች ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ አስረድተዋል፡፡

በተለይም ሐሙስ ሰኔ 01/2015 በጉጂ ዞን ቦሬ ሱኬ በተሰኘ ሥፍራ በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች እና አገረ ሰላም በተሰኘ ስፍራ በሚኖሩ የሲዳማ ተወላጆች መካከል በድንበር አቅራቢያ በተቀሰቀሰ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መጎዳታቸው ተነግሯል።

መሰል ችግሮች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ቢሆንም፤ በኹለቱም ክልሎች መንግሥታት በኩል የተወሰደ የመፍትሄ እርምጃ ባለመኖሩ በሰውና በንብረተ ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው ተብሏል።

የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልሽ ቶማስ “የብሔር ግጭት ተፈጥሯል የሚባለው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው፡፡” ሲሉ ጠቅሰው፤ “ግለሠብ ከግለሠብ ከተጋጨም ሰዎች ለራሳቸው ፖለቲካዊ ትርፍ  ሲሉ አጋነው ያወራሉ፡፡” ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም፤ ከዚህ ቀደም በሲዳማ ክልል ሥር በሚገኘው ወንዶ ገነት ወረዳ ኤዶ የምትባል ቀበሌ በሕዝበ ወሳኔ ወደ ክልሉ ከተካለለች በኋላ፤ አገራዊ ምክክር በሚደረግበት ወቅት ቁጥራቸው ሦስት የሚሆኑ የሲዳማ ክልል ተወላጆች “እኛን የማይወክሉ የጉጂ ኦሮሞ ተወላጆች ተመርጠዋል እኛ በምርጫው ውስጥ አልተካተትንም፡፡” በማለት ረብሻ ፈጥረው እንደነበር አውስተዋል።

ኮሚሽነሩ በመጨረሻም “ከእኛ አቅም በላይ የሆነ ችግር በክልላችን አልተፈጠረም፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።  

@Addis_News
@Addis_News