Get Mystery Box with random crypto!

~ ዘካቱል ፊጥር ~ ክፍል ሦስት ①ዘካቱል ፊጥር የሚሰጥበት ጊዜ መች ነው?? ዘካ | أبو سعيد

~ ዘካቱል ፊጥር ~
ክፍል ሦስት
①ዘካቱል ፊጥር የሚሰጥበት ጊዜ መች ነው??
ዘካቱል ፊጥር የሚሰጥበትን ጊዜ አስመልክቶ በዑለሞች መካከል በርካታ አቋሞች ቢስተዋሉም ከመረጃ አንፃር ጠንካራው አቋም እንደሚከተለው ነው

አንደኛ:—ዘካቱል ፊጥር መስጠት ፍቁድ የሚሆንበት ጊዜ ነው።ይህም ጊዜ ከኢዱ አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ያለው ጊዜ ነው።በዚህ መሰረት አንድ ሰው ዘካውን ከኢዱ አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን አስቀድሞ መስጠት ይችላል ማለት ነው።ይህም ተግባር ከሶሓቦች ተገኝቷል።ይህን አስመልክቶ የሚከተለው ዘገባ መጥቷል
عن ابن عمر قال " كانوا يعطونها قبل الفطر بيوم أو يومين" (رواه البخاري)
"(ሶሓቦች) ከፊጥር ( ከኢድ) በአንድ ወይም በሁለት ቀን አስቀድመው ( ዘካተል ፊጥርን) ይሰጡ ነበር " ( ቡኻሪ ዘግበውታል)

ሁለተኛ:—ዘካቱል ፊጥር መስጠት ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ።
ዘካቱል ፊጥር መስጠት ግዴታ የሚሆንበትን ጊዜ አስመልክቶ በኢስላም ሊቃውንቶች መካከል ሁለት አቋሞች የተንፀባረቁ ሲሆን ፤ የአብዛሃኛው ሊቃውንቶች አቋም ዘካቱል ፊጥር መስጠት ግዴታ የሚሆነው የረመዷን የመጨረሻው ቀን ፀሐይ ከጠለቀችበት ወቅት አንስቶ ነው የሚለው ነው።በዚህ አቋም መሰረት የረመዷን የመጨረሻው ቀን ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት የተወለደ ልጅ ፤ ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የሞተ ሰው እና ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት የሰለመ ሰው ላይ ዘካቱል ፊጥርን ማውጣት ግዴታ ይሆናል ማለት ነው።

ሦስተኛ: —ዘካቱል ፊጥርን ለመስጠት በላጩ ጊዜ ነው።
ዘካቱል ፊጥርን ለመስጠት በላጩ ጊዜ የሚባለው የኢዱ ዕለት ከኢድ ሶላት በፊት መስጠት ነው።ይህም የሆነው እንዲህ የሚል ሐዲስ ከመልዕተኛው ﷺ ስለተዘገበ ነው :—
عن اين عمر أن النبي " أمر أن تؤدى قبل خروج الناس إلى الصلاة "(رواه البخاري ومسلم)
ነብዩ ﷺ " (ዘካቱል ፊጥር) ሰዎች ወደ ሶላት ከመውጣታቸው በፊት እንድትሰጥ አዘዋል"
( ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

በዚህ ሐዲስ መሰረት በላጩ ጊዜ መልዕክተኛው ﷺ እንዲሰጥ ያዘዙበት ወቅት ነውና የምንችል ሰዎች ዘካችንን በዚህ ወቅት ብንሰጥ የተሻለ ይሆንልናል።

አራተኛ: —ከኢዱ ሶላት በኋላ ያለው ወቅት ነው።
ዘካውን ሆን ብሎ ከሶላት በኋላ መስጠት ሐራም የሆነ ተግባር ነው።እንዲሁም ዘካው እንደ ዘካተል ፊጥር እንደማይቆጠር ፍንትው ባለ ገለፃ ሐዲስ ላይ ተቀምጧል።ይህም :—
عن ابن عباس " فمن أداها قبل الصلاة فهي زكاة مقبولة، ومن أداها بعد الصلاة فهي صدقة من الصدقات"( أخرجه أبو داود وابن ماجاه)

" (ዘካተል ፊጥርን) ከሶላት በፊት የሰጠ እርሷ( ዘካዋ) ተቀባይነት ያላት ዘካ ናት፤ ከሶላት በኋላ የሰጠ እርሷ ከሶደቃዎች አንዷ ሶደቃ ናት "
( አቡ ዳዉድ እና ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል)

ስለዚህ ዘካችንን ከሶላት በኋላ የምንሰጥ ከሆነ ተራ ሶደቃ እንጂ ዘካተል ፊጥር አይሆንም ማለት ነው።
ማሳሰቢያ
✘አንድ ሰው በዑዝር ምክንያት ከሶላት በኋላ ቢሰጥ፤ ለምሳሌ መንገድ ላይ እያለ ነገ ኢድ መሆኑን ቢሰማና በራሱ ወይም በሰው አማካኝነት ዘካቱል ፊጥርን ማስተካከል እና ከሶላት በፊት መስጠት ባይችል ምንም ችግር የለውም።ከሰገደ በኃላ አስተካክሎ መስጠት ይችላል፤ ዘካውም እንደ ዘካተል ፊጥር ይቆጠርለታል።
✘የረመዷን የመጨረሻው ቀን ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ለተወለደ ልጅ ዘካ ማውጣት ግዴታ ነው ያልነው ከመወለዱ በፊት ለሱ ዘካ ማውጠት ተወዳጅ እንጂ ግዴታ አይደለም ብለን ከዚህ በፊት ስላየን ነው።
~ ወሏሁ ኣዕለም ~
ኢንሻአሏህ ይቀጥላል