Get Mystery Box with random crypto!

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ነሐሴ ፲፮ ❖ | ዘኆኅተ ብርሃን ሰንበት ት/ቤት (official) ቻናል

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ነሐሴ ፲፮ ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለእመቤታችን
#ቅድስት_ድንግል_ማርያም ዓመታዊ የትንሳኤና የዕርገት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ # ዕርገተ_ድንግል_ማርያም +"+

=>ይሕች ዕለት እጅጉን ታላቅና ክብርት ናት:: ምክንያቱም
የድንግል ማርያም ሥጋዋ ተነስቶ ዐርጐባታልና:: ድንግል
እመቤታችን ተነሳች: ዐረገች ስንል እንደ እንግዳ ደርሶ:
እንደ ውሃ ፈሶ: ወይም በአጋጣሚ የተደረገ አይደለም::
ጥንቱን በአምላክ ልቡና ታስቦ: ሁዋላም ትንቢት
ተነግሮለት ነው::

¤ታሪኩ: ነገሩ: ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም
በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት
እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::

+"+ የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ +"+

*ከአዳም በሴት
*ከያሬድ በሔኖክ
*ከኖኅ በሴም
*ከአብርሃም በይስሐቅ
*ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
*ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ
ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::

¤ከሌዊ ደግሞ በአሮን በአልዓዛር: ፊንሐስ:
ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::

¤አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በ5,485 ዓመት
ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት
ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ
ኢያቄምወሐና ትወለዳለች:: (ኢሳ. 1:9, መኃ. 4:7)
"ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ::
(ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ)

¤ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ3 ዓመታት ቆይታ ወደ
ቤተ መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ12
ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና
እያገለገለች: እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን
እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ: ጽዋዕ ሰማያዊ
እየመገቧት ኑራለች:: 15 ዓመት በሞላት ጊዜ ጻድቅ
አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::

¤በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና
ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው::
ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር:
ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ::
(ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)

¤ወልደ እግዚአብሔርን ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ጸንሳ:
እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14)
"#ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በናዝሬት ገሊላ ለ2
ዓመታት ቆዩ::

¤አርዌ ሔሮድስ "እገድላለሁ" ብሎ በተሳበት ወቅትም
ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም:
በዕንባና በኃዘን ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ከገሊላ እስከ
#ኢትዮዽያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን 5 ዓመት ከ6 ወር
ሲሆነው: ለርሷ ለድንግል ደግሞ 21 ዓመት ከ3 ወር
ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::

¤በናዝሬትም ለ24 ዓመታት ከ6 ወራት ልጇን ክርስቶስን
እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች::

እርሷ 45 ዓመት: ልጇ 30 ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን
ተጠምቆ በጉባኤ ትምሕርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ3
ዓመታት ከ3 ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም
እያደረች ትምሕርቱን ሰማች::

¤የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም
የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን
ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: (ሉቃ. 2:35) ጌታ
በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሳኤውን አየች::
ለ40 ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::

¤ከልጇ ዕርገት በሁዋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን
ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮን
ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ15 ዓመታት ኖረች::
በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ:
ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና:
ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::

¤ዕድሜዋ 64 በደረሰ ጊዜ ጥር 21 ቀን መድኃኒታችን
አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን
ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም
በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት
ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ:
ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ:
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ" እንዲል::

¤ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም
እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው
ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት:-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ:
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ:
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::

¤በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ
ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው) እነርሱን ቀጥቶ
እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር
አኑሯታል::

በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለ205 ቀናት
ቆይታለች::

¤ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን
ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ 1 ሱባኤ
ጀመሩ:: 2ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል
ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም
#በጌሴማኒ ቀብረዋታል::

¤በ3ኛው ቀን (ነሐሴ 16) እንደ ልጇ ባለ ትንሳኤ
ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሳኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ
ቅዱስ ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም
መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ
1 ቀን ሱባኤ ገቡ::

¤ለ2 ሳምንታት ቆይተው: በዚህች ቀንም ሁሉንም ወደ
ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ
የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ
ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን
ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት
ተመልሰዋል::

=>ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና #እመቤታችን:
ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን:
ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን::

ምንጭ፡ ዝክረ ቅዱሳን