Get Mystery Box with random crypto!

ስለምን 'ሀገር የመሆን' ጉዳይ ሲነሳ ፥ ከአማራ ብሔርተኛ ነኝ ባዩ ውስጥ ሳይቀር 'ብርድ ብርድ ፥ | ዘሪሁን ገሠሠ

ስለምን "ሀገር የመሆን" ጉዳይ ሲነሳ ፥ ከአማራ ብሔርተኛ ነኝ ባዩ ውስጥ ሳይቀር "ብርድ ብርድ ፥ ፍረሀት ፍረት" የሚለው ሀይል እንመለከታለን ?

ይህ የብሔርተኝነት ፅንሰ ሀሳብን በሚገባ ካለመረዳት የሚመነጭ ችግር ነው!

ብዙ ጊዜ " የአማራ ብሔርተኝነት የሀሳብ ጥራት ችግር አለበት!" እላለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አብዘሀኛው ብሔርተኛ ሀይል ብቻውን ተቀምጦ " ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ" እያለ ሲያጨበጭብ ፥ ሀገር የተዋቀረችበት አማራ ጠል ከሆነ ትርክት የተወለደው የፅንፈኞች ብሔርተኝነት ፥ አድጎና ጎልምሶ ብሎም መንግስታዊ ስልጣን ጭምር ይዞ ፥ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ሊያጠፋው ከጫፍ ሲደርስና የተጋረጠበት የህልውና አደጋ አፍጥጦ ሲመጣበት ፥ ግልፅና የጠራ የሀሳብ መስመር ሳያበጅ ፥ "በእውር ድንብርብር ራሱን ለማዳን ተገዶ የገባበት የማታገያ ስልት" ስለሆነ ብቻ ነው፡፡

ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኃላ ብሔርተኝነት/nationalism የፖለቲካ ማደራጃ ሆኖ መስፋፋት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ በርካታ አዳዲስ ሀገራት ተወልደዋል፡፡ የብሔርተኝነት ፈርጆች በርካታ ቢሆኑም ፥ በማንኛውም አይነት የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ፥ ፖለቲካዊ ትግል የጀመረ "የጋራ ማንነት ወይም መገለጫ አለኝ" ብሎ የተደራጀ የፖለቲካ ማህበረሰብ ፥ የትግሉ ማጠንጠኛዎች ፦ ከማንኛውም ውጫዊ ሀይል ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆንን ፥ ራስን በራስ የማስተዳደርና የራስ አስተዳደራዊ ግዛት (ሀገር) መፍጠርን ፥ …ሊያልፋቸው የማይችሉ ግልፅ መስፈርቶቹ አድርጎ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ማንኛውም የአማራ ብሔርተኛ " የአማራ ድንበሩ/ወሰኑ የት ነው?" ሲባል በቀጥታ የሚመልሰው መልስ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ቅዠትም በሉት ህልም ይህን ጥያቄ የኦሮሞ አለያም የትግራይ ብሔርተኞችን ስጠይቋቸው ያለማመንታት የሚመልሱት ፖለቲካዊ መልስ አላቸው፡፡ የአማራን ብሔርተኛ ስጠይቁት ደግሞ " የአማራ ድንበሩ ኢትዮጵያ ናት!" የሚል ረብ የለሽና እንደውም ፅንፈኞቹ "አሀዳዊያን ፥ ደፍጣጭ ፣ …ወዘተ" እያሉ ለሚከሱት ክስ ዋቢ የሚሆን መልስ ይመልሱልሀል፡፡

ይህ የብሔርተኝነቱ የሀሳብ ጥራት/ideal clarity ችግር የወለደው ነው፡፡ ይህ የአማራን ህዝብ ስርአታዊና መዋቅራዊ በሆነ መልኩ መከራ እያዘነበበት ያለው የሴራ ፌደራሊዝም ስርአት በዚሁ ከቀጠለና የአማራ ህዝብ የሚዘንብበት የመከራ ዶፍ "ሀገር አልባ" እስከማስባል በደረሰ ደረጃ እያዋረደው ከቀጠለ ፥ የአማራ ህዝብ መደራደሪያ የሚሆነው አለያም የመጨረሻ ውሳኔ የሚወስንበት ሁለተኛ አማራጩ "ሀገር" መሆን ነው፡፡

ይህን አስገዳጅ መስፈርት ሳያሰምሩ ልፍስፍስና ደካማ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ማድረጉ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝንና የመከራውን ዶፍ አባብሶ የሚያስቀጥል ይሆናል፡፡

እናም ኢትዮጵያ አማራው የግፍ ዶፍ ተሸክሞ እየተጨፈጨፈ ካለቀ በኃላ የሚወርሳት ጀነት ወይም መንግስተ ሰማያት አለመሆኗን የምታረጋግጥበት የሀሳብ መስመር ማስመር ግዴታ እንጂ ውዴታ አይደለም!

ይህ ከኢትዮጵያዊነት ማፈንገጥ ወይም ፅንፈኛ የመሆን አለያም የመጥበብ ጉዳይ ሳይሆን በማንኛውም አማራጭ የሀገር ባለቤትነትን የማረጋገጫ መሠረታዊ የፖለቲካ ነጥብ ነው!

ይኸው ነው!