2022-04-09 06:36:52
++ ‹‹እግዚአብሔር ያስታውሳል›› ++
በሉቃስ ወንጌል መጀመሪያ ላይ ታሪኩ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው ቤተሰብ የካህኑ ዘካርያስ ቤተሰብ ነው፡፡ በወንጌል መጀመሪያ ላይ የምናገኘው ይህ ካህን (በኦሪት መጀመሪያ ላይ እንደሚገኘው ካህን እንደ አሮን ሁሉ) የሚስቱ ስምዋ ኤልሳቤጥ ነው፡፡ (ዘጸ. 6፡23) ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ‹በሰው ፊት ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ› የሚሔዱ ሲሆን ልብንና ኩላሊትን በሚመረምረው ‹በእግዚአብሔር ፊት ደግሞ ጻድቃን ነበሩ› ይላል ወንጌሉ፡፡
ካህኑ ዘካርያስ እና ሚስቱ ኤልሳቤጥ እንደማንኛውም ባልና ሚስት ልጅ ለመውለድ የተመኙት በወጣትነታቸው ጊዜ ነበር፡፡ በተለይም ክህነት በዘር ሐረግ ብቻ በሚተላለፍበት በዚያ ዘመን ከአሮን የልጅ ልጅ ከአብያ ቤተሰብ የሆነው ዘካርያስ ወንድ ልጅ ወልዶ ልጁ እሱ በሚያገለግልበት መቅደስ ተተክቶ እንዲያገለግል ይመኝ ነበር፡፡ ይሁንና ሚስቱ ኤልሳቤጥ መካን ነበረች፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን መካንነት በወንድም በሴትም ሊከሰት ይችላል፡፡ ‹‹የተባረክህ ትሆናለህ ፤ በሰዎችህም ሆነ በእንስሳትህ ዘንድ ሴት ብትሆን ወይም ወንድ መካን አይሆንብህም›› የሚለው ቃል መካንነት በወንድም ሊከሰት እንደሚችል ያስረዳናል፡፡ (ዘዳ. 7፡14) በመጽሐፍ ቅዱስ ሰባት መካን ሴቶች ተጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም ሣራ ፣ ርብቃ ፣ ራሔል ፣ አንትኮዬ (የሶምሶን እናት) ፣ ሃና (የሳሙኤል እናት) ፣ ሜልኮል እና ኤልሳቤጥ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሰባት መካን ሴቶች ውስጥ ያልወለደችው የዳዊት ሚስት የሳኦል ልጅ ሜልኮል ብቻ ስትሆን ያልወለደችበት ምክንያት መካንነትዋ የመጣው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት የሚዘምረው ባልዋን ዳዊትን ስለናቀችውና አሽሙር ስለተናገረች ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ልጅ ባለመውለድ የተጠቀሰችው ሌላ ሴት ሱነማዊቷ ሴት ስትሆን ያለመውለድዋ ምክንያት በባልዋ ሽምግልና ምክንያት እንጂ በእርስዋ አለመሆኑ አብሮ ተጽፎአል፡፡ (2ነገሥ. 4፡14)
ኤልሳቤጥ ልጅ ካለመውለድዋ ይልቅ ትልቅ ስቃይ የሆነባት የሰዎች ነቀፌታ ነበር፡፡ በዚህ መሰቃየቷን የምንረዳው ከጸነሰች በኋላ እንኳን ጸነስኩ ብላ ለመናገር ተሳቅቃ አምስት ወራት ያህል ጽንሱን መሰወርዋ ነው፡፡ በእርግጥም ብዙዎች ከመካንነት በላይ ስቃይ የሚሆንባቸው የሰዎች ክፉ ንግግር ነው፡፡‹መቼ ነው የምትወልዱት?› ‹ትዳር ያለ ልጅ እንዴት ይሆናል?› ‹እስካሁን አልወለድሽም?› እየተባሉ በጥያቄ የሚቆስሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ አልፎ ተርፎም በአሽሙር የሚሰደቡ ፣ በነገር ጅራፍ የሚገረፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነን ጣውንትዋ ፍናና ታስቆጣትና ታበሳጫት የነበረችው ሃና ናት፡፡ ሃና ባለመውለድዋ በሚደርስባት ነቀፋ ምክንያት እህል እንኳን አስጠልቷት አትቀምስም ነበር፡፡ ደግነቱ ባልዋ ሕልቃና አለመውለድዋን አይቶ አልናቃትም ይልቁንም ‹‹ለምን ታዝኚአለሽ? ለምንስ እህል አትቀምሺም? ከአሥር ልጆች እኔ አልሻልሽም?›› ብሎ የሚያጽናና መልካም ባል ነበረ፡፡ (1ሳሙ. 1፡4-8)
ኤልሳቤጥም የገጠማት ይህ ዓይነቱ ፈተና ነው፡፡ መካን መሆንዋ ብቻ ሳይሆን የሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ ሚስት ሆና አለመውለድዋ የበለጠ ፈተና ነበር፡፡ ሰው መቼም በሰው ለመፍረድ ብዙ አይቸገርም፡፡ ‹ባልዋ በቤተ መቅደስ እያገለገለ እግዚአብሔር ልጅ የነሣቸው ክፉዎች ቢሆኑ ነው እንጂ›› ብሎ ማሰቡም አይቀርም፡፡ ዘካርያስ ካህኑ ግን በሚስቱ በኤልሳቤጥ ላይ አንዳች ክፉ ቃል አልተናገረም ፤ ተናግሮ ቢሆን ኖሮም ‹ሁለቱም ጻድቃን ነበሩ› ባልተባለለት ነበር፡፡ የሚገርመው ዘካርያስ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ፊት እንኳን ‹እኔ ሽማግሌ ነኝ ፤ ሚስቴም አርጅታለች› አለ እንጂ ስለ ‹ሚስቴ መካን ናት› ብሎ አንዲትም ቃል አልተናገረም፡፡
እነዚህ ጻድቃን ባልና ሚስት ልጅ ተመኝተው ባያገኙም ‹ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ› ይላል፡፡ ልብ አድርጉ ልጅ ሳይኖራቸው ፣ በኑሮአቸው ደስተኛ ሳይሆኑ በፈጣሪ ሕግና ትእዛዝ መሔድ መቻላቸው በጣም ከባድ ነው፡፡ በሰው ፊት ፈጣሪን ላለማማረር የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው በውስጣቸው ሊሳደቡ አልሞከሩም፡፡ ‹‹ምነው ፤ ምን አደረግንህ?›› እንኳን ብለው ፈጣሪያቸውን አልወቀሱም፡፡ በስቃይ ውስጥ ሆነው እንኳን ልብን በሚመረምረው አምላክ ፊት ‹ጻድቃን ነበሩ›፡፡ ቤት በልጆች ሳቅ ተሞልቶ ፣ ጤንነት ተሟልቶ ፣ ሀብት ንብረት ሳይጎድል እግዚአብሔርን ማምለክ ብዙ ላያስቸግር ይችላል ፤ በማጣት ፣ በመከራ ፣ በመሰደብ ውስጥ እየኖሩ ጻድቅ ሆኖ መገኘት ግን እጅግ አስደናቂ ነው፡፡
ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ ለመውለድ ፈጣሪን ሲማጸኑ ቢኖሩም የወጣትነታቸው ዘመን ግን አለፈ፡፡ ኤልሳቤጥ የሆድዋን ፍሬ ሳትመለከት ፣ ዘካርያስ የአብራኩን ክፋይ ሳያይ ፣ እንደ ካህናት ልማድ ልጁን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ሳይተካ ሁለቱም አረጁ፡፡ ‹‹እባክህ ፈጣሪ ሆይ ልጅ ሥጠን›› ብለው እየለመኑ ዓመታት አለፉ፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ግን ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ‹ዘካርያስ ሆይ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ልጅን ትወልድልሃለች› አለው፡፡ ዘካርያስ ግራ ገባው ፤ ከጸለየው ዓመታት ያለፈው ጸሎቱን ፣ ከተመኘው ዘመናት ያለፈው ምኞቱን አሁን ‹ተሰምቶልሃል› ሲባል ለደስታ አቅም አጠረው፡፡
ነቢዩ ዳንኤል ፈጣሪውን ሲለምን ወዲያው መልስ አልመጣለትም ነበር ፤ ከሃያ አንድ ቀን በኋላ ግን ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ‹ሰይጣን ከመንገድ አዘግይቶኝ ነው እንጂ ወደ አንተ የተላክሁት በዕለቱ ነበር› አለው፡፡ ዳንኤልም ሃያ አንድ ቀን ቢዘገይም እንኳን ገና ጸሎቱን አላቋረጠም ነበርና ከሦስት ሳምንት በኋላ የጸሎቱን መልስ ማግኘቱ ብዙም ግራ አላጋባውም፡፡ (ዳን.10፡12) ቅዱስ ገብርኤል ወደ ዘካርያስ መጥቶ ‹ጸሎትህ ተሰማ› ያለው ግን እንደ ዳንኤል ከሃያ አንድ ቀን በኋላ አይደለም፡፡ ከሃያ አንድ ዓመታት በኋላም እንኳን አይደለም፡፡ ዘካርያስ ሽማግሌ እስኪሆን ፣ ኤልሳቤጥም እስክታረጅ ድረስ ቆይቶ የወጣትነት ዘመኑን ጸሎት ነው ‹ተሰምቶልሃል› ያለው፡፡ ስለዚህ ዘካርያስ ‹ስእለቴ ሰመረ› ለማለት እንኳን ግራ ተጋባ፡፡
እግዚአብሔር አሠራሩ እንዲህ ነው ‹‹እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው እርሱ አይዘገይም።›› ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር መልስ የሚሠጥበት ጊዜ በሰው ሕሊና የሚመረመር አይደለም፡፡ (ዕን. 2፡3) የለመንነውን ነገር ሳያደርግልን ልናረጅ ፣ ልንሸመግል እንችላለን፡፡ ከዚያም አልፎ የተመኘነውን ነገር ሳይሠጠን ልንሞትም እንችላለን፡፡ ፈቃዱ ከሆነ ግን የጸሎታችንን መልስ ከመቃብር ቀስቅሶ ሊሠጠን ይቻለዋል፡፡ ይህን የማያምን ሰው ሙሴን መጠየቅ ይችላል፡፡
ሙሴ እግዚአብሔርን ‹ክብርህን አሳየኝ› ብሎ ለመነ ፤ እግዚአብሔርም ‹‹በዓለት ላይ አቆምሃለሁ ... ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን አታይም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ሙሴ ይህን እግዚአብሔርን ሳያይ ወደ መቃብር ወረደ፡፡ ሊሞት ሲል እንኳን ‹ያልከኝን ሳታሳየኝ› ብሎ ሳይጠይቅ የዋሁ ሙሴ ወደ መቃብር ገባ፡፡ በመቃብር ውስጥ ሆኖ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አሳለፈ፡፡ ከዘመናት በኋላ ግን ሙሴ በታቦር ተራራ ዓለት ላይ እንዲቆም ተጠራ፡፡ ‹ክብርህን አሳየኝ› ብሎ ለለመነው ልመና መልስ ተሠጠው፡፡ በታቦር ተራራ ‹አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር ያለውን ክብሩን አየ› የብሉይ ኪዳን ሰው ሆኖ ሳለ የሐዲስ ኪዳን ዕድል
138 views03:36