Get Mystery Box with random crypto!

አሜሪካ የራፋህን ጥቃት እንድታስቆም የፍልስጤሙ መሪ ተማጸኑ! የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ | YeneTube

አሜሪካ የራፋህን ጥቃት እንድታስቆም የፍልስጤሙ መሪ ተማጸኑ!

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እስራኤል ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በተጠለሉባት ደቡባዊ የጋዛ ከተማ ራፋህ ላይ ጥቃት ከማድረስ የምታስቆማት ብቸኛዋ አገር አሜሪካ ናት ብለዋል።ከፊል ዌስት ባንክን የሚያስተዳድሩት አባስ ማንኛውም የእስራኤል ጥቃት ፍልስጤማውያን ከጋዛ እንዲሸሹ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።እስራኤል በራፋህ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ደጋግማ እየዛተች ትገኛለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እሑድ ዕለት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት “በራፋህ ላይ ያላቸውን ግልፅ አቋም” በድጋሚ አስታውቀዋል።ሰላማዊ ዜጎችን ከጉዳት ለማዳን የሚያስችል አስተማማኝ ዕቅድ ካላየች በስተቀር አሜሪካ በራፋህ የሚካሄድን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መደገፍ እንደማትችል ደጋግማ ተናግራለች።በሳዑዲ ርዕሰ መዲና ሪያድ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ጉባዔ (ደብሊውኢኤፍ) ላይ ንግግር ያደረጉት አባስ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ አሳስበዋል።

"እስራኤል ይህን ወንጀል እንዳትፈጽም ማድረግ የምትችለው አሜሪካ ብቻ ስለሆነች እስራኤል የራፋህ ዘመቻዋን እንድታቆም እንድትጠይቅ አሜሪካን እንማጸናለን። ራፋህ ላይ የሚደረግ "ትንሽ የሚባል ጥቃት" ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለመሸሽ እንደሚያስገድድ ተናግረዋል።"በፍልስጤም ህዝብ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ጥፋትም ያኔ ይከሰታል።" ብለዋል።ከግማሽ በላይ የሚሆነው የጋዛ ህዝብ በራፋ የሚገኝ ሲሆን በከተማዋ ያለው ሁኔታም የከፋ የሚባል ነው። የተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ፣ የውሃ እና የመድሃኒት እጥረት እንዳለባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዋይት ሃውስ በራፋህ የሚካሄደውን ዘመቻ በተመለከተ ባይደን ለኔታንያሁ የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ በዝርዝር አልገለጸም። የብሔራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ለኤቢሲ እንደተናገሩት እስራኤል ወደ አካባቢው ከመግባቷ በፊት የአሜሪካን ስጋቶች እና ሃሳቦችን ለማዳመጥ ተስማምታለች።የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወደ ሪያድ አቅንተው ከአባስ ጋር ሊነጋገሩ መሆኑም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ተስፋ እየፈነጠቀ የመጣው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ የተኩስ አቁም ድርድር እና በጋዛ የቀሩትን ታጋቾች የማስለቀቅ ሂደት በእስራኤል ጥምር መንግሥት ውስጥ ያለውን መከፋፈል ይበልጥ እያጋለጠው ነው።

@YeneTube @FikerAssefa