Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመለመሉ የምርጫ ክልል አስፈፃሚዎችን በተመለከተ ፓርቲዎች ባቀረቡ | YeneTube

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመለመሉ የምርጫ ክልል አስፈፃሚዎችን በተመለከተ ፓርቲዎች ባቀረቡት ቅሬታ ላይ ውሳኔ ሰጠ!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ክልል ደረጃ ምርጫ ለማስፈጸም የመለመላቸውን የምርጫ አስፈጻሚዎች ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለት ዙር በማቅረብ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት በጠየቀው መሠረት ከ10 ፓርቲዎች የተሰጡ አስተያየቶችን መርምሮ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።

ከአስሩ መካከል ሦስት ፓርቲዎች ዝርዝር አስተያየት ያቀረቡ መሆኑን ነው ቦርዱ ያስታወቀው።

“የምርጫ አስፈፃሚው ገለልተኛ አይደለም” እና “የሌላ ፓርቲ አባል ነው” በማለት የቀረቡ አቤቱታዎች መኖራቸውን የገለጸው ምርጫ ቦርዱ፣ ያለምንም ማስረጃ የቀረቡትን አቤቱታዎች እንዳልተቀበለው አስታውቋል።

ነገር ግን የፓርቲ አባልነት የከፈሉ ማስረጃ የቀረበባቸውን አስፈጻሚ ከአስፈጻሚነት መሠረዙን በምሳሌነት አንስቷል።

“የምርጫ አስፈፃሚው የራሴ አባል ነው” በማለት ማረጋገጫ ያቀረበ ፓርቲ በአቤቱታው መሠረት አባላቶቼ ናቸው ያሉት ከአስፈጻሚነት እንዲሰረዙ ተደርጓል ብሏል።

“በዞናችን ላሉት ምርጫ ክልሎች የአስፈፃሚዎች ዝርዝር አልተላከም” በሚል ላቀረቡት ቅሬታ ደግሞ በሦስተኛው ዙር እንደሚላክ እንዲገለጽላቸው መወሰኑን ገልጿል።

“የማይታወቁ አስፈፃሚዎች ናቸው” በሚል ለቀረበው ቅሬታ የምርጫ ቦርድ የኦፕሬሽን ክፍል አድራሻቸውን አጣርቶ በሦስተኛው ዙር እንዲልክ እንዲደረግ ተወስኗል ነው ያለው።

“የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን እና ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለሥልጣን ከመጡ ዝርዝሮች ውስጥ ምልመላው መከናወን አልነበረበትም” የሚል አቤቱታ የቀረበ መሆኑን እና ተቋማቱ የመንግሥት ተቋማት በመሆናቸው ብቻ የሚመለመሉ ሰዎች ዝርዝር መካተት የለበትም የሚለውን ውሳኔ ቦርዱ እንዳልተቀበለው አሳውቋል።

@YeneTube @FikerAssefa