Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት፡፡ ልባም ልጆችዋ አጥር ሆነው የጋረዷት፣ ዋጋ ከፍለው ያደመቋት፣ ተቆ | ጋፋት ስቱዲዮ / Gafat Studio

ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት፡፡ ልባም ልጆችዋ አጥር ሆነው የጋረዷት፣ ዋጋ ከፍለው ያደመቋት፣ ተቆጥሮ በማያልቅ መሥዋዕትነት ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገር ናት፡፡ የሩቁ ቢዘነጋን እንኳን፣ አምና ጥቅምት 24 ግፍ የተፈጸመባቸው ጀግኖቻችን ታሪክ ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም፡፡ እያንዳንዳችን የጀግኖቹ ዕዳ አለብን፡፡ ዛሬ የቆምነው ለእኛ ሲሉ የግፍ ጽዋን በተጎነጩ ጀግኖቻችን አጥንት ላይ ነው፡፡ እነዚያ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች “ከወገኔ በፊት እኔ ልቅደም” ብለው ደማቸውን ለአፈር፣ ሥጋቸውን ለአሞራ ባይሰጡ ኖሮ የዛሬው ቀን ዛሬን ባልመሰለ ነበር፡፡

የሰሜን ዕዝ ሠራዊት የተደራጀው ከአንድ አካባቢ አልነበረም፡፡ አማራና ኦሮሞው፣ ሲዳማና ወላይታው፣ አፋርና ጋምቤላው፣ ጉራጌና ሐድያው ከሁሉም ብሔር ተውጣጥቶ ሀገር እንዲጠብቅ የተደራጀ ሠራዊት ነበር፡፡ ሀገሬን ብሎ ለሃያ ዓመታት ከቤቱና ካሳደገው ቀዬ ተነጥሎ ዱር እያደረ ድንበር ሲጠብቅ ኖሯል፡፡ ሠራዊቱ ለትግራይ ክልልና ለሕዝቡ ከደግነት ውጭ ክፉ ሆኖ አያውቅም። ጠላት ሲመጣ የሚመክት፣ አዝመራ ሲደርስ የሚያጭድ፣ በማኅበረሰባዊ ተግባራት ላይ የሚካፈል ነበር። በደምና በላቡ ለከፈለው ደግነት በምላሹ ከሽብር ቡድኑ ሕወሐት የተቀበለው ክህደት ነው።

ኢትዮጵያን ለመውረር የመጡ ጠላቶች እንደ ሽብር ቡድኑ ዋነኛ የጦር ቤዛችንን በመደብደብ አልጀመሩም፡፡ ዋና ዋና መኮንኖችን በመግደልና ከባድ መሣሪያዎቻችንን ዘርፈው አልተነሡም። የጦርነት ቅዱስ ባይኖርም ለጭካኔም ልክ አለው። በሽብር ቡድኑ ልክ ኢትዮጵያ ላይ የጨከነ የለም፡፡ ጥቅምት 24 ሠራዊቱ ላይ የክህደት ጥቃት ሲፈጸም የሞቱት እነዚያ ጀግኖች ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ እንደመሆናቸው የተፈጸመባቸው ግፍ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመ ግፍ ነው።

የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት መሣሪያ ለመዝረፍ ብቻ የተደረገ ተራ ጥቃት አልነበረም፡፡ በተንኮል የተቀመመና በክፋት የሞላ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ የገዛ ጓዶቹን አስኮብልሎ በተኛበት ከመግደል ባለፈ ከሬሳው ላይ ልብሱን ገፍፎ የአውሬ ቀለብ እንዲሆን እርቃኑን ሜዳ ላይ ጥሎታል። ይኼን ሲያደርግ የሽብር ቡድኑ ዓላማ ሁለት ነው፡፡ አንደኛ ሠራዊቱ በሐፍረት በትር እየተቀጣ ሞራሉ እንዲላሽቅና የአቅመ ቢስነት ስሜት እንዲሰማው፡፡ ሁለተኛ ሠራዊቱ እርስ በእርስ እንዳይተማመንና “ክፉና ደጉን አብሮ ከተካፈሉኝ ጓዶቼ እንደዚህ ዓይነት ነውር ዛሬ ከተፈጸመብኝ ነገስ?” ብሎ እንዲጠራጠር ለማድረግ ታስቦ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ሠራዊቱ እንደተጠበቀው አልሆነም፡፡

የወንድሞቹ ደም በከንቱ መፍሰስ ያንገበገበው ሠራዊት በፍጥነት ራሱን አደራጅቶ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሽብር ቡድኑ ያደራጀውን ኃይል ወደ በርሃ እንዲበተን ማድረግ ችሏል፡፡ የቡድኑን ቁንጮ አመራሮች አብዛኞቹን ይዞ ለሕግ አስረክቧል፡፡ የተፈጸመበትን ክህደት በበቀል ሒሳብ ሳይሆን የሕግ ማስከበር መርሕን በተከተለ መንገድ ሲያከናውን ነበር፡፡ በጦርነት ውስጥ ለመርሕ መገዛት ቀላል አይደለም፡፡ ሠራዊታችን ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከሽብር ቡድኑ ጋር አያሌ ውጊያዎችን ሲያደርግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በየጦር ውሎው በጀግንነት እየተዋጋ ለእናት ሀገሩ ተሠውቷል፡፡ ለሀገርና ለወገን ያለውን አጋርነት በንግግር ሳይሆን በተግባር አሳይቷል፡፡ አሁንም በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ነው፡፡

ዛሬ ሽብር ቡድኑ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንድ እድል ከመጠቀም ይልቅ እንደ ድል ወሰደው። በአማራና በአፋር ክልል በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የግፍ በትሩን ቀጥሎበታል፡፡ የጥፋት አጋሩ ሸኔም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ልዩ ልዩ አደጋዎችን እየጣለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ረፍት እየነሣ ነው፡፡ ሌሎችም የጥፋት ኃይሎች ከውስጥም ከውጭም ወኪሎቻቸውን አስተባብረው በሙሉ ዐቅማቸው ኢትዮጵያ ላይ መዝመታቸውን ገፍተውበታል፡፡

ሠራዊታችን ብቻውን ተጋፍጦ የድል ዜና እንዲያበስረን መጠበቅም ሞኝነት ነው፡፡ ጠላቶቻችን ተባብረው የደቀኑብን አደጋ ሁላችንም ተባብረን ካልመከትነው ድል የማይታሰብ ነው፡፡ የጠላቶቻችን ኅብረት ለፕሮፓጋንዳ የተፈበረከ ጉዳይ አይደለም፡፡ እውነት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ዓላማቸው ግልጽ ነው፡፡ ብረት ያነሡት ሀገር ለማፍረስ እንጂ ሀገር ለመገንባት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ስም በክፉ የሚያብጠለጥሉ፣ ነገ የሊቢያና የሶርያን እጣ ሊያስታቅፉን እንዲመቻቸው የፈጠሩት ዘዴ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ጠላቶቻችን በዚህ ደረጃ ሲተባበሩብን እኛ አንድ የማንሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የወንድምና የእኅቶቹ ጥቃት የሚያንገበግበው ሁሉ ጣት ከመጠቆም ወጥቶ ሀገር የማዳን ፍላጎቱን በተግባር መግለጥ አለበት፡፡

ወደፊት ታሪክ ፍርዱን ይሰጣል፡፡ ፈሪውም በፈሪነቱ፣ ሴረኛውም በሴረኛነቱ እንደየግብሩ ይመዘገባል፡፡ የሽብር ቡድኑን ትውልድ በክህደት ሲያስታውሳቸው እንደሚኖር ግልጽ ነው፡፡ በተቃራኒው በግፍ የተሠውት የሰሜን ዕዝ አባላትን ጨምሮ ለሀገር የሚዋደቁ ጀግኖች ስማቸው በወርቅ ይጻፋል፡፡

ክብር ኢትዮጵያን ሲሉ ለተሠዉ ጀግኖቻችን!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ታማኝ፣ ትኩስ፣ ወቅታዊና ሚዛናዊ መረጃዎችን ለመከታተል እንዲሁም ቶሎ ቶሎ እንዲደርሳችሁ የቴሌግራም ቻናላችን ቤተሰብ ይሁኑ!

ድል ለአማራ ህዝብ
ድል ለእናት ሀገራችን
ሞት ለአሻባሪው እና ለመላው ሀገር ሻጮች

ቻ @YeNatnael_Tube
ና @YeNatnael_Tube
ል @YeNatnael_Tube

መረጃዎችን ለመለዋወጥ የቴሌግራም ግሩፑን ይቀላቀላሉ @AmharaDiscussion