2021-10-16 07:02:10
ብር ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተምሯቸው 3ቱ ነገሮች
1. ስለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ፡- ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ልጆቻቸው ስለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ያስተምሯቸዋል፡፡ የገንዘብን ዋጋን እና ገንዘብ እንዴት እንደሚገኝ እንዲያውቁ ይጥራሉ፡፡ ከልጅነታቸው ለቤት ውስጥ አገልግሎት ወይም ለመሳሰሉት ስራዎች አነስተኛ የኪስ ገንዘብ በመስጠት ሰርቶ ገንዘብን ማግኘትን እና መቆጠብን ያስተምሯቸዋል፡፡ በተጨማሪም ገንዘብ በጥረት እና ያገኘናቸውን እድሎች በአግባቡ በመጠቀም የሚገኝ እንጂ በቀላሉ የማይገኝ መሆኑን እንዲረዱ ያደርጋሉ፡፡
2. ምንም ነገር ይገባኛል ብለው እንዳያስቡ ይመክሯቸዋል፡- አንዳንድ ሰዎች ነገሮች ለኔ ሊሰጡ ወይም ለኔ ሊሆኑ ይገባል ብለው ያስባሉ፡፡ እንደዚህ የሚያስቡ ሰዎች ራሳቸውን ለማሻሻል ወይም ገንዘብ ለማግኘት መስራት እና መሮጥ አይፈልጉም፡፡ ማንም ምንም አይሰጠኝም እኔው ለራሴ ራሴን መቻል አለብኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ግን ይሮጣል፤ ይጥራል፡፡
ገንዘብ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት ይሄንን ነው፡፡ ያላቸው ሃብት ልጆቻቸውን ለማስተማር ወይም ቢዝነስ ለማስጀመር ሊጠቅም ቢችልም ልጆቻቸው ጠንክረው ያላቸውን ነገር ለማሳደግ መጣር እንዳለባቸው ካልሆነ ግን ገንዘብ ጠፊ መሆኑን ያስረዷቸዋል፡፡ አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን በፌት እንዳለው “ አንድ ሃብታም ሰው ለልጆቹ መተው ያለበት ገንዘብ፤ ስራ የሚያሰራ እንጂ ገንዘቡ በዝቶ ቁጭ የሚያደርጋቸው መሆን የለበትም፡፡”
3. ነገሮች በተአምር ወይም በፍጥነት እንደማይቀየሩ ያስተምሯቸዋል፡- ብዙዎቻችን በፍጥነት (ነገ ጠዋት) ህይወታችን የሚቀየር ይመስለናል፡፡ እንደዛ የሚሆንላቸው ጥቂቶች ቢኖሩም ባብዛኛው ህይወታችን የሚቀየርው በጥረት እና በዘመን ውስጥ ነው፡፡ ቅዱስ መፅሃፉም እንደሚለው በችኮላ የምትከማች ሃብት ትጎድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸ ግን ትበዛለች፡፡
ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን ስኬታማ ካልሆኑ ሰዎች የሚለያቸው ዋናው ነገር ስኬታማ ሰዎች አርቆ አሳቢ መሆናቸው ነው፡፡በተቻላቸው መጠን የተለያዩ እቅዶች ለሚቀጥለው አመት፤ አምስት አመት፤ አስር አመት እያሉ ያወጣሉ፡፡ እቅዶቻቸውን ከዳር ለማድረስም ይሰራሉ፡፡ በዛ ላይ በውስጣቸው ተአምራት ስለማይጠብቁ ስሜታቸው በቀላሉ አይጎዳም፡፡ ይሄንን የማቀድ፤ አላማ እና ግብ ማስቀመጥን እና ግብ ለመምታት መጣርን ወላጆች ለልጆቻቸው ያስተምራሉ፡፡
@yehasab_menged
@yehasab_menged
623 viewsTeddy, 04:02