Get Mystery Box with random crypto!

ፍቅራችን በእውቀትና በማተዋል ይብዛ ወደ ፊልጵስዩስ 1: 9-11 9-11፤ ለእግዚአብሔርም ክብር | Yeka Abado Full Gospel Belivers'church

ፍቅራችን በእውቀትና በማተዋል ይብዛ

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 9-11

9-11፤ ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።

1. ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሆን ዘንድ ከክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶብን መገኘት አለብን:: እናስተውል ከእኛ አይደለም የጽድቁ ፍሬ የሚመጣው ከጠራን ከራሱ ነው:: ነገር ግን ገና የራሳችንን ጽድቅ ለማቆም የምንነሳ ከሆነ አስቸጋሪ ነው ወደ እረፍቱ መግባታችን ታድያ ምኑ ላይ ነው? ውላችን እኛ ልንሞት እርሱ በእኛ ሊኖርም አይደል? እንደዛ ካላሰብን የምንፈልገውን መለወጥ አናየውም ጥረት ግረት ሆኖ ይቀራል:: ክርስትና ግን እረፍት ነው ደግሞም ክብርና ምስጋናን ከእኛ ህይወት የተነሳ የምናመጣ ነን:: ደስ አይልም? በተቃራኒውም እንዳለ ልብ እንበል::

2. ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ እኛ የመድኃኒታችንን ከሰማይ መገለጥ የምንጠባበቅ ነን:: ስንጠባበቅ ግን ኑሮ እናቆማለን ማለት አይደለም ነገርን ፈትነን የሚሻለውን ማለትም:- እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ይለናል ቃሉ:: ይህንንም የምናደርገው ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅተን ቅኖችና እለነውር ሆነን እንጠብቅ::

3. ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። ፍቅር በእውቀት እየጨመረ የሚመጣ ነው:: ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ ጌታ ይፈልጋል:: ይህ እንዲበዛ ነው ጳውሎስ እጸልያለሁኝ ያለን እኛም እንጸልይ ይህ ከመታወቅ የሚያልፍ ፍቅር በህይወታችን ውስጥ ይገኝ ዘንድና ማስተዋልም እንዲሆንልን::