Get Mystery Box with random crypto!

መልካሙን ስራ ክርስቶስ ይፈጽመዋል ወደ ፊልጵስዩስ 1: 3-8 3-5፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ | Yeka Abado Full Gospel Belivers'church

መልካሙን ስራ ክርስቶስ ይፈጽመዋል

ወደ ፊልጵስዩስ 1: 3-8

3-5፤ ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ።

6፤ በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤

7፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል።

8፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና።

የዝች ቤተክርስቲያን ሰዎች ከጳውሎስ ጋር ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ነው አብረውት የወንጌል ሰራተኛ የሆኑት እርሱም በጣም ነው የሚወዳቸውና ስለእነሱ ሲጸልይም በደስታ አምላኩን ያመሰግናል::

ጳውሎስ ወዳጅነቱን በግልጽ ነው የሚያሳየው ደብዳቤው የግል እንጂ ለቤተክርስቲያን የተጻፈ መልእክት እንኳን አይመስልም:: ባደረጉለት ስጦታ ምክንያት ህይወቱን ይደግፉ ነበርና መቼም ድንኳን በመስፋት ብዙውን ጊዜ ከሚያውል ለማገልገል እንዲችል አስችለውታል ምክንያቱም አብራችሁኝ አገለገላችሁ ብሎ እውቅና እየሰጣቸው ነው:: ጸጋ የተለያየ ነውና በተሰጠን ጸጋ እንገለጥ ያን ጊዜ ወንጌል በኃይል ይሄዳል የግድ ሁሉም ሰው መስበክ የለበትም ልግስናም ጸጋ ነውና ለመንግስቱ ያስፈልጋል:: የተሰጠን ጸጋ ምንድነው? እናገልግልበት::

እግዚአብሔር ታማኝ ነውና በእናንተ የተጀመረው ስራ ይቀጥላል፥ ይሰፋል ምክንያቱም እሱ የታመነ ጌታ ስለሆነ የስራውም ባለቤት እርሱ ስለሆነ ይህ የማይቀር ሀቅ ነው:: በእርግጥ የእኛ መተባበር ያስፈልጋል የእግዚአብሔር ግን መምራትና መርዳት አስፈላጊ ነው እርሱንም ያደርገዋል እያለን ነው ለእኛም።

በእስራቱ ሳያፍሩና ሳይረሱት ስለእርሱ በማሰብ አብረውት ቆመዋል ከዚህ ሁሉ በላይ ግን እንደዚህ ያቆመው ጸጋ እንደሆነ ጳውሎስ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው ለእናንተም ይህ ጸጋ ያቆማችኃል እያላቸው ነው:: ምንም አይነት ነገር ቢመጣ እርሱ በጸጋው ያቆማችኃል እኔ ምስክር ነኝ እያለ ነው::

ዛሬም በምናልፍበት ሁሉ በጸጋው ሊረዳን የታመነ ነው የእኛ ጌታ ከጳውሎስ ጋር እንደነበረ ዛሬም ከእኛ ጋር በስራ ላይ ነው::
ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች ከመውደዱ የተነሳ ሁልጊዜ መቼ ነው የማያቸው በሚል ጉጉት ውስጥ ነበር ግን የወንጌል ስራ ስለበለጠበት ሳያያቸው ቆየ:: ሊያያቸው እንዴት እንደሚናፍቅ ግን እግዚአብሔር ነው ምስክሬ ይላቸዋል እንዲህ ያለ መነፋፈቅንና መተሳሰብን ጌታ በዘመናችን ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥም ያድርግ ይህ ፍቅር ይፍሰስልን:: አሜን!