Get Mystery Box with random crypto!

የኦሮሚያ ባንክ 43.5 ቢሊዮን የሚሆነውን በብድር መልክ ማቅረቡን አስታወቀ። ከተመሰረተ 15 ዓመ | TIKVAH-MAGAZINE

የኦሮሚያ ባንክ 43.5 ቢሊዮን የሚሆነውን በብድር መልክ ማቅረቡን አስታወቀ።

ከተመሰረተ 15 ዓመታት ያስቆጠረው ኦሮሚያ ባንክ በዛሬው ዕለት የፋይናንስ አቅርቦቱ በፈጠው የሥራ እድል ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው እንደተጠቀሰው 54 ቢሊዮን ብር በቁጠባ መልክ ማሰባሰቡን፤ ከዚህ ውስጥም 43.5 ቢሊዮን የሚሆነውን በብድር መልክ ማቅረቡን አስታውቋል።

ከፍተኛ የደንበኞች ቁጥር ካላቸው ባንኮች በ5ኛ ደረጃነት የተቀመጠው ባንኩ በብድር አሰጣጥ ዙሪያ የሰራቸው ሥራዎች አብነት የሚሆኑ መሆኑን አንስቷል።

በተለይም ዝቅተኛ የብድር አቅርቦት በመስጠት ብድርን ተደራሽ በማድረግ በኩል ጥሩ የሚባል ልምድ መኖሩን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን ገልጸዋል።

የባንኩ የብድር አቅርቦት ምን ይመስላል?

ባንኩ ለብድር ካቀረበው 43.5 ቢሊዮን ብር 26 በመቶ የሚሆነውን ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በብድር አቅርቧል። ይህም በነፍስ ወከፍ ሲሰላ በአማካይ አንድ ተበዳሪ 1.5 ሚሊዮን ብር ከባንኩ ማግኘቱ ተገልጿል።

ቀሪው የብድር አቅርቦት ለከፍተኛ ተበዳሪዎች የቀረበ ሲሆን የዚህም አማካይ የብድር አቅርቦት በአማካይ አንድ ተበዳሪ 5 ሚሊዮን ብድር መውሰዱ ተገልጿል።

የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ስንት ነው?

የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ስንት ነው ተብለው ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዝዳንቱ፥ የባንኩ የተበላሸ የብድር መጠን በዘርፉ ካለው ቁጥር የተሻለ መሆኑን አንስተዋል።

በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት የተበላሸ ብድር መጠን ጣሪያ 5 በመቶ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ አሁን ላይ በዘርፉ ያለው አማካይ የተበላሸ የብድር መጠን 3.6 በመቶ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ባንክ የተበላሸ የብድር መጠኑ ከ1.6 በመቶ እስከ 2 በመቶ የሚደርስ እንደሆነ ጠቅሰው ይህም ባንኩ የሚሰጣቸው ብድሮች ጤናማ ለመሆናቸው ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

በመግለጫው ተጨማሪ ምን ሀሳቦች ተነሱ

- ባንኩ በገላን ከተማ ለሚያስገነባው የልኅቀት ማዕከል እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚያስገነባው የዋና መስሪያቤት ግንባታ ጋር  ከ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት እያከናወነ ነው።

- ባንኩ አሁን ላይ ከ10 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውቋል። ከዚህም ውስጥ 6,550 የሚሆኑት ቋሚ ናቸው።

- አሁን ላይ ቅርንጫፎችን ከመክፈት ወደ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት ፊቱን ማዞሩን ገልጾ በዚህም "ኦሮ ዲጂታል" በተሰኘው አገልግሎት ቴሌግራምን ጨምሮ በ7 አማራጮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

- ከ8 ቢሊዮን በላይ ከወለድ ነጻ አገልግሎት በቁጠባ መሰብሰቡን ገልጾ ከዚህ ውስጥ ወደ 6 ቢሊዮን የሚሆነውን ለደንበኞቹ በብድር መልክ ማቅረቡን ገልጿል።

#OromiaBank #Economy

@TikvahethMagazine