Get Mystery Box with random crypto!

በካናዳ መንግስት ቀረበ የሚባለው የሥራ  እድል #ሐሰተኛ ነው። በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የካ | TIKVAH-MAGAZINE

በካናዳ መንግስት ቀረበ የሚባለው የሥራ  እድል #ሐሰተኛ ነው።

በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የካናዳ መንግስት ለ40,000 ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን (ቁጥሩ ሊለያይ ይችላል) የስራ እድል እየሰጠ ነው የሚል መረጃ ተመልክተዋል?

ይህ #ሐሰተኛ መረጃ አሁን ላይ በተለይ በፌስቡክ ላይ በተለያዩ ጉሩፖች አንዲሁም ገጾች ላይ ተለጥፎ በስፋት የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ሙሉ የሚሞሉ ፎርሞች፣ ሀሰተኛ ደብዳቤዎች አብረው ተያይዘው ተለቀዋል።

በተጨማሪም ከታዋቂ ሰዎች ፎቶዎች ጋር ተደርጎ ሲለቀቅ ተመልክተናል። ይህ መረጃ ሀሰተኛ እንደሆነ በአቀራረቡ ቢያስታውቅም ቀላል የማይባል ሰው ግን እየተሸወደ ይገኛል።

ለመሆኑ ማስታወቂዎቹ ምን ይላሉ?

ለኢትዮጵያዊያን እና ለኤርትራዊያን የተባለው ይህ የሥራ ዕድል አመልካቾች ቢያንስ 20 ዓመት የሆናቸው፣ የመኖሪያ መታወቂያ ያላቸው እና ቢያንስ 10ኛ ክፍል ወይም ከዚያ በላይ ያሟሉ መሆን አለባቸው ይላል። በተጨማሪም አመልካቾች ፖስፖርት እንዲኖራቸው ይጠይቃል።

ከዚህ ሐሰተኛ መረጃ ጀርባ ያለው ጥቅም ምንድን ነው?

በእነዚህ ማስታወቂያዎች ከተጠቀሱት ስልክ ቁጥሮች መካከል ለአንደኛው እንደደወለ የነገረን የቤተሰባችን አባል ለአጠቃላይ ሂደቱ ከሚያስፈልገው 400 ሺ ብር ቅድሚያ 10 በመቶ የሚሆነውን እንዲከፍል መጠየቁን ገልጿል።

እነዚህ ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ የቢሯቸውን አድራሻ ለመግለጽ እንዳልፈለጉ በደፈናው "ቢሯችን ቦሌ ነው" ብለው እንደገለጹለት ጠቅሶ በርካታ የሥራ እድል መኖሩን በቅድሚያ ግን የታደሰ ፖስፖርት ያስፈልጋል እንዳሉት ገልጾልናል።

በእነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች የተመለከትናቸው የስልክ ቁጥሮች ብቻ ሲሆኑ ቋሚ አድራሻ አልተጠቀሰም። ስልክ ቁጥሮቹም የተለያዩ እንዲሁም በርከት ያሉ ናቸው። ይህም ይህንን ዘዴ ተጠቅሞ ለማጭበርበር የሚፈልጉ ሰዎች መበራከትን ያሳያል።

የካናዳ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ምን ምላሽ ሰጠ?

የካናዳ ኢሚግሬሽን፣ ስደተኞች እና ዜግነት ጉዳዮች ቃላቀባይ ኤሪን ከርቤል " መረጃው ሐሰተኛ ነው፤ እንደዚህ አይት ፕሮግራም አልጀመርንም" ሲሉ ለፔሳ ቼክ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። እንደዚህ አይነት የሥራ እድል በተቋሙ ትክክለኛ ዌብሳይት ላይም አለመለቀቁንም አንስተዋል።

ህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በምን በኩል?

መንግስት የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን በተመለከተ ህገ- ወጥ ደላላሎች እና ኤጀንሲዎችን ማጭበርበር ያስወግዳል ያለውን የዲጂታል ሲስተም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል በማበልጸልግ ወደ ትገበራ መግባቱ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት E-LMIS ድህረገጽ ላይ አንድ ሚሊየን ሥራ ፈላጊ ሰራተኛ  መመዝገባቸውን በቅርቡ አስታውቋል። በተጨማሪም በዚህ ሥርዓት አማካኝነትም በሙሉ የመንግስት ዋስትና በቀን 1800 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን #በነፃ ወደ ውጭ ሀገራት እየተላኩ ናቸው ሲል ጠቅሷል።

#FakeNewsAlert
#StaySafeOnSocialMedia

@TikvahethMagazine