Get Mystery Box with random crypto!

በሐረርና ጅግጅጋ አካባቢ የተተከሉት ትራንስፎርመሮች በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ተባለ። የሐረርና የጅግ | TIKVAH-MAGAZINE

በሐረርና ጅግጅጋ አካባቢ የተተከሉት ትራንስፎርመሮች በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ተባለ።

የሐረርና የጅግጅጋ ከተሞችና አካባቢያቸውን ችግር እንዲፈቱ የተተከሉት ፓወር ትራንስፎርመሮች ተከላ እና የፍተሻ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለሙከራ ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንዳስታወቁት÷ በሐረር ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር የፓወር ትራንስፎርመር ተከላ ሥራ እና ፍተሻው በመጠናቀቁ ኃይል መስጠት የሚችልበት የሙከራ ሥራ የሚሰራበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

አዲሱ የፓወር ትራንስፎርመር መሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ በሐረር፣ በአወዳይ፣ በኮምቦልቻ ከተሞችና የገጠር መንደሮች በማከፋፈያ ጣቢያው በሚስተዋለው ከአቅም በላይ ጭነት ምክንያት ያጋጥም የነበረውን የኃይል እጥረት ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እስከ ሐሮማያ ከተማ እንደ አስፈላጊነቱ መመገብ የሚችል አቅም የተፈጠረለት ሲሆን÷ አዲሱ ትራንስፎርመር ከነባሩ ትራንስፎርመር አቅም ጋር ሲነጻጸር በ5 እጥፍ የሚበልጥ አቅም እንዳለው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በጅግጅጋ ማከፋፈያ ጣቢያ የፓወር ትራንስፎርመር ተከላ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን÷ አፈጻጸሙም ከሐረር ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር ተቀራራቢ በሆነ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሪጅኑ የሰብስቴሽን ኦፕሬሽንና ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከድር አብደላ ገልጸዋል።

አቶ ከድር አክለውም÷ ሪጅኑ ከሑርሶ እስከ ሐረር ድረስ ባለው የ132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ላይ አስራ ሁለት የ132ኪሎ ቮልት 400/800/1 አምፐር ከረንት ትራንስፎርመሮችን በመትከል የምስራቅ ኢትዮጵያን የግሪድ ሲስተም የሚያስተካክል ሥራ ሰርቷል ብለዋል፡፡

@tikvahethmagazine @tikvahmagbot