Get Mystery Box with random crypto!

የዒድ አከባበር ደንቦች ክፍል 3 ከዒድ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ስህተቶችን በተመለከተ ከክፍል | 🗞 ጣሀ አህመድ – Taha Ahmed 🗞

የዒድ አከባበር ደንቦች

ክፍል 3

ከዒድ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ስህተቶችን በተመለከተ ከክፍል ሁለት የቀጠለ

ኛ. ባዕድ በሆኑ ወንዶችና ሴቶች መካከል መቀላቀል፤ አልፎም መጨባበጥና መሳሳም፡፡ ይህ ሸሪዓው ክፉኛ የኮነነው ተግባር ነው፤ የአላህ መልእክተኛ (ሰላትና ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን) ከእለታት አንድ ቀን ከመስጂድ በመውጣት ላይ ሳሉ ወንዶች ከሴቶች ጋር በመንገድ ላይ ተቀላቅለው ተመለከቱ ይህንን ክስተት በማስመልከትም "ከወንዶች ወደ ኋላ ሁኑ፤ የመንገዱንም መሀከል ይዛችሁ ልትጓዙ አይገባም" አሉ፡፡ ይህንን ሀዲስ የዘገበው ሰሃቢይ "ከዚህ በኋላ ሴቶች በጣም ወደ ዳር ከመውጣታቸው ልብሳቸው በአጥር ይያዝ ነበር፡፡" በማለት ይናገራል፡፡(አቡዳውድ ሱነናቸው ላይ ሲዘግቡት አልባኒ ሀሰን የሚል ደረጃ ሰጥተውታል) ይህ ሀዲስ ሸሪዓ በጥቅሉ ወደ ሀራም የሚያደርሱ ነገሮችን የከለከለ መሆኑን ከሚያሳዩ መረጃዎች አንዱ ነው፡፡
በሌላ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (ሰላትና ሰለም በርሳቸው ላይ ይሁን) "እኔ ሴቶችን አልጨብጥም" ማለታቸው ሰፍሯል፡፡ ሀዲሱ አንድ ሰው ምንም እንኳ የተቀደሰ አላማና ንፁህ ልቦና ነው የያዝኩት ቢልም ባዕድ ሴቶችን ከመጨበጥ ሊቆጠብ እንደሚገባ የሚያመለክት ነው፡፡
ኛ. እንደ ሙዚቃ እና መሰል የተከለከሉ ነገሮችን ከማድመጥ፣ ፊልሞችን በመመልከት ጊዜን ከማጥፋት መቆጠብ ያስፈልጋል:: እንዲሁም ሌሎችንም ሀራም የሆኑ ተግባራትን በሙሉ መጠንቀቅ ይገባል::
ኛ. በዒድም ይሁን በሌላ ጊዜ በኢስላም ማባከን እጅጉን የተኮነነ ተግባር ቢሆንም በዒድ እለት በአንዳንዶች ዘንድ ከሚታዩት ስህተቶች መካከል ምግብና መጠጥን ማባከን ነውና ልንርቀው ይገባል::
ኢስላም በራሱ የተሟላ ነው!
እንደሚታወቀው ሀይማኖታችን ኢስላም ምሉዕ ነው፡፡ ስለሆነም ለሁሉም የአምልኮ ዘርፎች እንዲሁም የህይወት መስኮች ደንቦችን ደንግጓል ስርዐቶችንም አስቀምጧል፡፡ ሕግጋቶቹ ፍትሀዊ እና ሚዛናዊ ስርዐቶቹም ለሁሉም ቦታ እና ዘመን የሚበጁ ናቸው፡፡ አላህ (ሱብሀነሁ ወተአላ) እንዲህ ይላል:-
{الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا} المائدة 3

‹‹ዛሬ ሐይማኖታችሁን ሞላሁላችሁ፤ ፀጋዬንም በእናንተ ላይ ፈፀምኩ፤ ከሀይማኖት በኩልም ለእናንተም ኢስላምን ወደደኩ...›› (አልማኢዳ፡ 3)
ከዚህም በመነሳት መጨመርንም ይሁን መቀነስን አይቀበልም እንዲሁም ከሌሎች መኮረጅንም ሆነ መመሳሰልን ይከለክላል፡፡
ይህንን እዉነታ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላምና ሰላት በርሳቸው ላይ ይሁን) በነዚህ ሁለት ነብያዊ አስተምህሮቶች ይገልፁታል፡፡

قال رسول الله صلى الله عليه وسلم : ( من أحدث في أمرنا هذا ما ليس منه فهو رد ) رواه البخاري (2697) ومسلم (1718)

"በዚህ በዲናችን ላይ ከርሱ ያልሆንን ያመጣ (ሰው) ስራው ተመላሽ ነው፡፡ (ተቀባይነት አይኖረውም)" (ቡኻሪ እና ሙስሊም ዘግበውታል)

قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : ( مَنْ تَشَبَّهَ بِقَوْمٍ فَهُوَ مِنْهُمْ ) رواه أبو داود (4031)

"ከህዝቦች የተመሳሰለ እረሱ ከነርሱ ነው፡፡" (አቡ ዳውድ ዘግበውታል)
ስለሆነም ዒዳችንን ስናከብርም ይሁን ማንኛውንም አይነት ዒባዳ ስንፈጽም ከጭማሪ (ቢደዓ) እራሳችንን ልናርቅ እንዲሁም በማነኛውም የህይወታችን ክፍሎች ከሌሎች ጋር መመሳሰልን ትተን ሙሉ የሆነውን ሸሪዓን በማወቅ ወደ ተግባር ልንለውጥ ይገባል::

تقبل الله منا ومنكم صالح الأعمال.

አላህ መልካም ስራችንን ይቀበለን!!

*ጣሀ አህመድ (1431ሂ) የተፃፈ*


https://t.me/tahaahmed9