Get Mystery Box with random crypto!

የዒድ አከባበር ደንቦች ክፍል 2 የተክቢራ አፈፃፀም ከመልክተኛው ትክክለኛ ሰነድን መሰረት | 🗞 ጣሀ አህመድ – Taha Ahmed 🗞

የዒድ አከባበር ደንቦች

ክፍል 2

የተክቢራ አፈፃፀም

ከመልክተኛው ትክክለኛ ሰነድን መሰረት ያደረገ እና የተክቢራን አባባል ዝርዝር ሁኔታ የሚገልፅ መረጃ ባይገኝም ከሰሀቦቻቸው ግን "አላሁ አክበር አላሁ አክበር ወሊላሂልሀምድ" እና የመሳሰሉት አባባሎች በትክክለኛ ሰነድ ተዘግበዋል፡፡ ስለሆነም ሙስሊሞች እነዚህን አባባሎች የትኞቹ እንደሆኑ ማጥናትና እነርሱን ማዘውተር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢብኑ ሀጀር አል-ዓስቀላኒ ፈትሁል-ባሪ በተሰኘው ኪታባቸው እንዲህ ይላሉ "በዚህ ዘመን (ተክቢራን በተመለከተ) ብዙ መሰረት የሌላቸው ጭማሪዋች ተከስተዋል፡፡" ይህ በሂጅራ አቆጣጠር (ከ773-852) የኖሩት የኢስላም ሊቅ ንግግር ነው። ታዲያ ባለንበት ዘመን ምን ያህል ጭማሪ ተከስቶ ሊሆን እንሚችል ስናስተውል በጉዳዩ ላይ ከባድ ጥንቃቄ ልናደርግ እንደሚገባ ያመላክተናል፡፡
በአንድ ድምፅ ወይም አንድን ሰው አዝማች (አውጪ) ሌላው ተቀባይ ሆኖ የሚደረግ ተክቢራም ሱናን የሚቃረን ተግባር ነው። በዚህ ዙሪያ ተምሳሳይ ድርጊት ከሚፈጽሙት ወገኖች እንደ መረጃ የሚጠቀሰው የዑመር ተግባር (ሚና ላይ በድንኳን ውስጥ ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ተክቢራ ሲያደርግ ሰዎችም ተክቢራውን ሰምተው ተክቢራን ማድረጋቸው) የሚያመለክተው የእሱን ድምፅ ሲሰሙ ተክቢራን ማድረግ እንዳለባቸው በማስታወስ እነርሱም ተክቢራ ያደርጉ እንደነበረ እንጂ ሌላን አይደለም። ስለሆነም ይህ ክስተት፤ በጋራ ድምፅ እርሱን እንደ አዝማች እነርሱ እንደ ተቀባይ ሆነው ይቀጥሉ ነበር የሚለውን እንድምታ አያስጨብጥም ሲሉ ዑለማዎች ይናገራሉ፡፡

ጥቂት ከዒድ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ስህተቶች

ኛ. ዒድ መሆኑ ከታወቀበት ሰአት ጀምሮ ወንዶች ከሰላተል ጀመዓ መቅረት ብሎም በረመዳን ሲሰግዱት የነበረውን ዊትር ሰላት ማቋረጥ፤ አንዳንዴም አምልኮዎች በዚህ ያበቃሉ የተባለ ይመስል እርግፍ አድርጎ መተው ይስተዋላል፡፡
ኛ. የዒዱን ዋዜማ ለሊት በተለያዩ ዒባዳዎች ህያው ማድረግን በተመለከተ የመጡት ሀዲሶች ከሰነድ አንፃር ደካማዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ለሊቱን በተለያዩ የሚጠቅሙም ይሁን ያማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ማሳለፍ፤ በዚህም የተነሳ የፈጅር ሰላትን አለመስገድ እና ሰላተል-ዒድን እንደ ቀላል በመመልከት ችላ ብሎ መተው::
የዒድ ሰላትን በተመለከተ "ሰላተል-ዒድ በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ በነፍስ ወከፍ ግዴታ ነው" የሚለው የአቡ ሀኒፋ አቋም ሲሆን ከኢማሙ አሻፊዒይ እና አህመድም ከተዘገቡት ሁለት የተለያዩ አቋሞች አንዱ የሚጠቁመውም ይህንኑ ነው። ሸይኹል-ኢስላም ኢብኑ-ተይሚያህ እና ሌሎች ብዙ ዑለማዎችም ይህን አቋም የሚደግፉ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ኛ.በአለባበስና መቆነጃጀት ዙሪያ ከሚከሰቱ ስህተቶች መካከል ብዙ ወንዶች ፂማቸውን መላጨትና ማሳጠር እንዲሁም ልብሳቸውን ከቁርጭምጭሚታቸው በታች እነዲወርድ በማድረግ የሚፈፅሙት ስህተት ይገኝበታ። ሴቶች ደግሞ ሽቶን በመቀባት በመገላለጥ የሚፈፅሙት ስህተት እጅግ አደገኛ ነው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ የመጡት ነብያዊ አስተምህሮቶች በጣም አስፈሪና አስደንጋጭ ናቸው፡፡

عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ عَنْ النَّبِيِّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ قَالَ : ( مَا أَسْفَلَ مِنْ الْكَعْبَيْنِ مِنْ
الْإِزَارِ فَفِي النَّارِ) رواه البخاري (5787)

ከአቡሁረይራ በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል:- "ከሽርጥ ከቁርጭምጭሚት የወረደዉ የእሳት ነው" (ቡኻሪና በቁጥር (5787) ዘግበዉታል)
ይህ ሁሉንም የልብስ አይነት እንደሚያካትት ለመግለፅ አል-ኢማም አል-ቡኻሪይ ለሀዲሱ "ከቁርጭምጭሚት የወረደው እሱ የእሳት ነው" የሚል ርዕስ ሰጥተውታል።
በሌላ ሴቶች ከቤት ሲወጡ ምን አይነት ስነ-ስርአት መከተል እንደሚገባቸው በሚጠቁም ሀዲስ ላይ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል:-"ማንኛዋም ሴት ሽቶን ተቀብታ ወደ መስጂድ የወጣች እንደሆነ እስክትታጠብ ድረስ ሰላቷ ተቀባይነት የለውም፡፡"(ኢብኑ ማጃህ እና አህመድ ዘግበውታል አልባኒም ሰሂህ መሆኑን ገልፀዋል፡፡)

عن أبي هريرة قال: قال صلى الله عليه وسلم : "صِنفانِ مِن أهلِ النارِ لم أرَهما..... ونِساءٌ كاسياتٌ عارياتٌ مميلاتٌ مائلاتٌ، رؤوسُهُنَّ كأسنِمَةِ البُخْتِ المائلةِ لا يَدْخُلْنَ الجنةَ ولا يَجِدْنَ رِيحَهَا، وإن رِيحَهَا لَيوجَدُ مِن مَسيرةِ كذا وكذا". رواه مسلم(2128)

ሙስሊም አቡ ሁረይራን ዋቢ አድርገው ባስተላለፉት ሀዲስ ላይ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል:- "ከእሳት ሰዎች መካከል ሁለት አይነት ሰዎች በእኔ (ዘመን) አላየኋቸውም (ወደፊት ይመጣሉ)" አሉና፤ የመጀመሪያዎቹ ምን አይነት ባህሪ እንዳላቸው ካብራሩ በኋላ "ሌለኞቹ ሴቶች ናቸው፤ ለብሰው ያልለበሱ አካሄዳቸው እና እንቅስቃሴያቸው ወደርካሽ አላማ ያዘነበለ፤ ሌሎችንም የሚያሳስቱ ፀጉራቸው ልክ እንደ ግመል ሻኛ የተከመረ ናቸው:: እንደነዚህ አይነቶቹ ጀነትን አይገቡም ሽታዋንም አያገኙትም" አሉ::

ክፍል 3 ይቀጥላል.…

*ጣሀ አህመድ (1431ሂ) የተፃፈ*

https://t.me/tahaahmed9