Get Mystery Box with random crypto!

ʺአልደርቅ ያሉ የደም ቦዮች፣ አባሽ ያጡ እንባዎች' እልፍ እንባዎች ፈስሰው፣ እልፍ ጊዜ ከንፈር | Raya kobo communication

ʺአልደርቅ ያሉ የደም ቦዮች፣ አባሽ ያጡ እንባዎች"

እልፍ እንባዎች ፈስሰው፣ እልፍ ጊዜ ከንፈር ተመጥጧል፣ ቁጥሩ የማይታወቅ ሻማ ተበርቷል፣ ነጭ መብሩቅ ተወልቆ ጥቁር ማቅ ተጠልቋል፣ ሙሾ ተደርድሯል፣ ለቅሶ ተለቅሷል፤ የንፁሐን ሞት እልፍ ጊዜ ተወግዟል፣ ዳሩ የሻማው መብዛት፣ የከንፈር መምጠጡ መበርከት፣ ከሞት አላዳነም፣ እድሜ አልቀጠለም፣ ሰላም አላመጣም፡፡ አንደኛው ሻማ ሲጠፋ ሌላ ሻማ እየተበራ፣ የሞት ወግ በየቡናው እንደ ልማድ እየተወራ ቀናት አለፉ፣ ሳምንታት ከነፉ፣ ዓመታት ተከታተሉ፡፡
እናት ከጡቶቿ ተለይተው ስለሞቱ ልጆቿ ያለ ማቋረጥ ታነባለች፣ ከእቅፏ ተነጥለው የሰይፍ እራት ስለሆኑ የአብራኳ ክፋዮች የደም እንባ ታፈስሳለች፣ ወገቧን በገመድ አሥራ ትኖራለች፣ ዙሪያዋን በክፉ አድራጊዎች ተከባ ኤሎሄ ወይ ፍረድ ትላለች፣ ለጭንቄ ድረሱ ስትል ትጣራለች፣ ያጠለቀችውን ማቅ አላወለቀችም፣ የምታፈስሰውን እንባ አልገደበችም፣ ለማልቀስ እንጂ ለመሳቅ አልታደለችም፣ ስለሞቱት ልጆቿ እያለቀሰች፣ ስለ ቀሩት ልጆቿ ሕይወት ትንሰፈሰፋለች፣ የክፉ እጆች ቀሪ ልጆቿን ይቀስፍባታልና፡፡
ከሰይፍ ተርፈው የቀሩት ልጆቿን እንዳታጣቸው ትሰጋለችና፡፡

ትናንት ያለፈው አልፏል፣ ለነገው አይደገምም ተብላ ሌላ ሞት መጥቶ ልጆቿን ሲወስድባት፣ ባለቤቷን ሲነጥልባት፣ ጎረቤቷን ሲለይባት ተመልክታለችና፤
ዛሬም በቀሩት ላይ ክፉዎች እንደማይነሱ ማረጋጋጫ የላትም፡፡ ለዚያም ነው በስጋት የምታለቅሰው፡፡

ቀባሪ እስኪጠፋ ድረስ በአንድ ላይ ሄደዋል፣ በአንድ ጀንበር አልቀዋልና፡፡ መንገዳቸው ፊትና ኋላ አልሆነም፤ ብዙዎች በአንድ ቀን ላይመለሱ ሄዱ እንጂ፡፡ አስታምሞ መቅበር ብርቅ ሆኖባቸው፣ ዘመድና ወገን አቃብሩኝ ብሎ መጥራት ርቋቸው መኖር ግድ ብሏቸዋል፡፡
የሚያለቅሱት፣ ጥቁር ለብሰው ጥቁር ዘመን የሚያሳልፉት፣ እንባ እንደ ዥረት የሚያፈስሱት፣ አርሰው፣ አፍሰው የሚበሉ፣ አርሰው አፍሰው የሚያበሉ፣ ሐጥያት ያልተገኘባቸው፣ በደል የሌላቸው፣ በማንም ላይ ያልዘመቱ፣ በማንም ላይ ነፍጥ ያላነሱ ንፁሐን ናቸው፡፡

አርሰው በሚበሉበት፣ በሬና ገበሬ በአንድ ላይ በማሳ በሚውሉበት፣ ማሳው ተለስልሶ ዘር በሚበተንበት በክረምት ያላሰቡት ውርጅብኝ ወረደባቸው፣ የሞት ጥላ ጋረዳቸው፣ የእንባ ማዕበል አጥለቀለቃቸው፡፡ የተረፉት በክረምት ሸሹ፣ ከሞቀ ቤታቸው፣ ከሚወዷት ቀያቸው ተለይተው ነብሳቸውን ለማትረፍ ኳተኑ፡፡ ልጆች ከእናታቸው ጡት እየተነጠቁ ተሰዉ፣ ይድኑ ዘንድ መጠለያ ፈልገው በቤት የተደበቁ በክፉዎች እጅ እየታደኑ አለፉ፡፡ ፈሪ ሰው ነፍጥ የያዘውን ሸሽቶ በባዶ እጁ የተቀመጠውን ይገድላል፤ አፈሙዝ ወደ ያዘው አይተኩስም፣ ኾኖሎት አይዋጋም፤ ነገር ግን እርፍና ሞፈር የያዘውን ይገድላል፡፡ በኢትዮጵያን ባሕል ሞትን ሽሽት እንኳን ከቤቱ ከዛፍ ስር የተጠለለ ሰው ላይ ነፍጥ አይነሳም፣ ተተኩሶ አይገደልም፡፡ ጀግኖች ሀገር ሊያጠፋ የመጣ ጠላት እንኳን ፈርቶ ከዛፍ ስር ተጠልሎ እንዳይገድሉት ከጠያቀቸው አፈሙዛቸውን ያነሳሉ፣ ጎራዴያቸውን ወደ ሰገባቸው ይመልሳሉ፡፡ ለምን የተጠለለ አይገደልምና፤ የጀግና ወጉ ፊት ለፊት የገጠመን ገድሎ ማሸነፍ ነውና፡፡

ፈሪዎች ግን ልጇን የታቀፈችን እናት፣ ሞፈርና ቀንበር ተሸክሞ በሬዎችን የሚነዳ አባት፣ በሜዳው ያለ ክፋት የሚቦርቁ ሕጻናትን፣ ለፈጣሪያቸው ምሕላና ምልጃ የሚያደርሱ አዛውንቶችን በግፍ ይገድላሉ፣ የንጹሐንን ደም በግፍ ያፈስሳሉ፣ በሃይማኖት ተቋማት የተጠለሉ ንጹሐንን የሃይማኖታዊ ክብሩን ንቀው፣ የሰብዓዊነት ከፍታውን አዋርደው ያሻቸውን ያደርጋሉ፡፡ ንፁሐንን ገድሎ የክፉዎች ምድር መፍጠር ይሆን? ወይንስ በንፁሕ ደም ደስታን መሻት ይሆን? ዓላማቸው አይታወቅም፡፡ ቀን እየጠበቁ የንጹሐንን ደም ያፈስሳሉ፤ ቤት ያፈርሳሉ፣ ያልሰሩበትን ንብረት ይወርሳሉ፡፡

በንጹሐን እልቂት ብዙዎች አንብተዋል፣ በድርጊቱ ተሸማቅቀዋል፣ ብዙዎች አውግዘዋል ነገር ግን እንባው፣ ማውገዙና ማዘኑ የሚሞቱትን አላዳናቸውም፡፡ ሌላ ሞት እንዳይኖር ጠበቃ አልሆናቸውም፡፡ ከሰሞኑ የሽብር ቡድን ታጣቂዎች በምዕራብ በወለጋ ጊምቢ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት ብዙዎች ላይመለሱ አሸልበዋል፤ በስቃይ ውስጥ አልፈዋል፡፡ እናት እና ልጅ ተለያይተዋል፣ በግፍ ከመጣው ሞት የተረፉ አዛውንቶች ጧሪ አጥተዋል፡፡ ከአንድ ቤተሰብ ውሰጥ ብዙዎች አልፈዋል፡፡

አልደርቅ ያሉ የደም ቦዮች፣ አባሽ ያጡ እልፍ እንባዎች ተበራክተዋል፡፡ ከዛሬ ነገ ይደርቃል፣ ሰላም ይመጣል፣ አጥፊዎች ቢቻል ልብ ገዝተው ካልተቻለ ራሳቸው ጠፍተው ንጹሐን አርሰውና አፍሰው የሚበሉበት፣ በሰላም የሚኖሩበት ዘመን አልደርስ ብሏል፡፡ ዜጎች ያለ እረኛ እንደ ተለቀቁ በጎች ተኩላው ከጎሬው እየወጣ እየበላቸው፣ ያለ ዘመናቸው እየወሰዳቸው ነው፡፡ የዜጎች እረኛም በአጥፊዎች ላይ በትሬን እያሳረፍኩ ነው ቢልም አጥፊዎች ደግሞ በንጹሐን ላይ በትራቸውን ማሳረፋቸውን አላቆሙም፡፡

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች በኢትዮጵያውያን ላይ እግራቸውን በሚያነሱ ጠላቶች ሁሉ እርምጃ ይወስዳል፡፡ ያለ እረፍት ይደክማል፣ ግን ዛሬም ሙሉ ለሙሉ ጠላቶቹን ማጥፋት አልቻለም፡፡ በጥላቻ የተገነባ ቡድን ተግባሩና ዓላማው ጥላቻ ብቻ ነው፡፡ ጥላቻ ልቡን ካጠፋው ቡድን ንጹሐንን ለማትረፍ ብስለት የተመላበት መንገድ መሄድ መልካም ነው፡፡

ማልቀስና መወቃቀስ ብቻ ንጹሐንን ከሞት አያድናቸውም፣ ማውገዝ ብቻም አያተርፋቸም፣ ንጹሐንን ከሞት ለማትረፍ እኔስ ምን አደረኩ? በምን መልኩ ኀላፊነቴን ተወጣሁ ? ማለት ግድ ይላል፡፡ የንጹሐን የደም ቦይ እንዲዘጋ፣ የግፍ ሞትም እንዲቀር በአንድነትና በብልሃት መነሳት፣ የጋራ ጠላትን በጋራ መቅጣት፣ ከፍ ሲልም ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ አንሁን በጋራ ለሚገድለን ጠላት በተናጠል አንወቃቀስ። አሁን የመወቃቀሻ ዘመን አይደለም፣ በአንድነት ቆሞ፣ በአንድነት ድል አድርጎ መኖርን ማረጋገጥ እንጂ፡፡
ጠላቶችን አጥፍቶ ንጹሐንን ለማትረፍ እንትጋ፣ ዜጎች የማይሳደዱበት፣ በቀያቸውና በመንደራቸው የሚኖሩባት፣ ሰላምና አንድነት የሰፈነባት ሀገር ትኖር ዘንድ ዛሬ እንነሳ፡፡ ክፉ ልምድ ክፉ ነው፣ በሁሉም በር እየደረሰ የሞት መርዶ ይነግራልና፡፡

በታርቆ ክንዴ (አሚኮ)