Get Mystery Box with random crypto!

የራያ ቆቦ ወረዳ ወቅታዊ ምልእክት ====================== ሶለል የባህላችን ፈርጥ !! | Raya kobo communication

የራያ ቆቦ ወረዳ ወቅታዊ ምልእክት
======================
ሶለል የባህላችን ፈርጥ !!!
===============
ባህል ይወረሳል፣ ባህል ያድጋል ፣ ባህል ይዳብራል፣
ባህል ይሞታል ።
የሚያድገው የሚያሳድገው ማህበረሰብ ሲያገኝ ፤ የሚወረሰው የሚወርስ ተተኪ ሲኖር ነው ። በአንፃሩ ደግሞ የሚሞተው የሚንከባከበውና የሚከታተለው ማህበረሰብ ሲያጣ ነው ።

በራያ ቆቦ ከሚከበሩ ባህላዊ ሃይማኖታዊ ይዘት ካላቸው በአላት አንዱ ሶለል ነው ። ሶለል ከቅድመ አያቶቻችን የወረስነውና በየአመቱ ሳይቆራረጥ በልጃገረዶች የሚቀነቀን ጣእመ ዜማ ያለው ባህላዊ ሁነት ነው።

የሶለልን በአል አከባበርና ታሪካዊ አመጣጥ ስንቃኝ ሶለል በየአመቱ ከነሃሴ 16 ጀምሮ የሚከበር በአል በመሆኑ በአሉ ከመድረሱ ከ 5 ቀን በፊት ከ10-15 ቁጥር ያላቸው ቡድኖች ይደራጁና አለቃና ገንዘብ ያዥ ይመርጣሉ ።

ቆነጃጅቶች ጋሜና ቃሪሳ ፣ ጎበዝና ቆንጆ ፣ አንድ እግራና አፈሳሶ በሚባሉ የፀጉር ስሬቶች አምረውና ተውበው ቅድመ ዝግጅቱን ያጧጡፉታል ።

በሌላ በኩል ለሶለል የተመለመሉ ወጣት ሴቶች ባህላዊ አልባሳትን እንደ" ትፍትፍ"በተለያዩ ክሮች ያሸበረቀ" ሽራጦና መቀነት" ባህላዊ ጌጣጌጦች "ድኮት" በማጥለቅና ከእናቶቻቸው ያገኙትን "የብርድንብል" በደረታቸው ላይ ጣል አድርገው ጧት የወጣች ጀንበር መስለው ወደ በአሉ ይቀላቀላሉ ።

በበአሉ ቀን ማለዳ ተነስተው ከተቆጣጠሩና ለውበታቸው እርስበርስ አስተያየት ከተሰጣጡ በኋላ በመጀመሪያ የእድሜ ባለፀጋ የሆኑ አዛውንቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ቤት በመሄድ በመረዋ ድምፃቸው ሶለልን ያንቆረቁሩታል ።

ሆኖም የዚህ በአል አከባበር ሂደት በ 2013 አ/ ም ክረምት ራያ ላይ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠበት ሁኔታ በመፈጠሩና አሁንም ከጦርነት ስነ-ልቦናና እሳቤ ያልወጣንበት ወቅት ቢሆንም ባህሉን ለማሳደግና ባህላዊ ፈርጥነቱን ይዞ ዘመን እንዲሻገር ለማድረግ በዚህ አመት "ሃገር በቀል እውቀት ለተሻለ ማህበረ ኢኮኖሚ ፖለቲካዊና ባህላዊ እድገት" በሚል መሪ ቃል ይከበራል ።

ይህም ባህሉን ለትውልድ ለማስተላለፍ ብሎም በአለም የቅርስ መዝገብ እንዲመዘገብ የማድረግ አንዱ ተግባር ነው ።

ይህ ብቻውን ያለ ህብረተሰቡ እና የባለድርሽ አካላት ሚና ዋጋ ስለማይኖረው እንደተለመደው ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል።
ስንል መልእክታችንን እናስተላልፋለን !!!

* ሶለል የባህላችን ፈርጥ ነው !!!
* ባህልን ማሳደግ የሁሉም ህብረተሰብ ሃላፊነት
ነው !!!

የራያ ቆቦ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት
ሃምሌ 21/2014
ቆቦ