Get Mystery Box with random crypto!

በጥንት አበው ዘመን “አማኝ ነኝ” የሚል ሁሉ በርግጥ የመዳኑና የመለወጡ ምልክት የግል ፍተሻ (se | ቅኔ እና ዜማ / QINE ENA ZEMA official

በጥንት አበው ዘመን “አማኝ ነኝ” የሚል ሁሉ በርግጥ የመዳኑና የመለወጡ ምልክት የግል ፍተሻ (self-examination) እንዲያደርግ፣ የሽማግሌውና የተወዳጁን ሐዋርያ ዮሐንስን መልእክት ቱንቢ አድርገው ይጠቀሙበት እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያስረዳል። በዚያ ሚዛን የት ይሆን ያለነው - ማለት በሰው ፊት ሳይሆን በጌታ ፊት? የእግዚአብሔር መንግሥት መዝገብ ሳይውቀን፣ በቤተ ክርስቲያን መኖርና ማገልገልም ይቻላል። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነውና! በቤቱ ውስጥ እንክርዳድም አለ። መከር በሚታጨድበትና እውነተኛው ሰብል ከእንክርዳዱ በሚለይበት ዘመን እራሳችንን የት እናገኝ ይሆን? በዚህ ምድር በጌታ ቤት ዘመን ቆጥሮ፣ ምስባኩ ላይ ታይቶና ደምቆ፣ በላይ ግን፣ “ከቶ አላወቅኋችሁም”፣ መባልን ከመሰማት የምናመልጠው አሁን ቀን ሳለ በእግዚአብሔር ፊት በእውነት በመኖር ነው! እስቲ በሐዋርያው ዮሐንስ “የእግዚአብሔርና የዲያቢሎስ ልጆች" ልዪነት መለኪያዎች፣ በግርድፉ ለቅመን ባወጣናቸ 31 መስፍርት እራሳችንን እንይ። ልብ እንበል፣ ዮሐንስ የጻፈው ለአማኞች ነው። “እንግዲህ ልጆች ሆይ፤ እርሱ ሲገለጥ ድፍረት እንዲኖረን፣ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።” (1 ዮሐ. 2:28)።

1) እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም . . . በጨለማ እየተመላለስን ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል እንዋሻለን፤ እውነትንም አንኖረውም።(1ዮሐ. 1፡5-6)

2) ኀጢአት የለብንም ብንል [በዚህ ምድር በራስችን ፍጹም - perfectionism) ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም (1ዮሐ. 1:8)

3) “እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም (1ዮሐ. 2፡4)

4) ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል። (1ዮሐ. 2:6)

5) በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው (1ዮሐ. 2:9-11)

6) ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ (1ዮሐ. 2:15)

7) ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ ወልድን የሚያምን ሁሉ አብም አለው። (1ዮሐ. 2:23)

8) ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ። - (1ዮሐ. 2:29)

9) ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ዐመፅን ያደርጋል፤ ኀጢአትም ዐመፅ ነው . .በእርሱም የሚኖር ኀጢአትን አያደርግም (ሁን ብሎ ልቡ እያወቀ - perpetual, habitual and intentional sinning) ፤ ኀጢአት የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም አላወቀውም። (1ዮሐ. 3:4-6)

10) ኀጢአትን የሚያደርግ (perpetual, habitual and intentional sinning) ከዲያብሎስ ነው:: ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ አንሥቶ [እስከ አሁን] ኀጢአትን የሚያደርግ ነው (1ዮሐ. 3:8)

11) ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአትን አያደርግም፤ የእርሱ ዘር በውስጡ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደም ኀጢአትን ሊያደርግ አይችልም። (1ዮሐ. 3:9)

12) የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፦ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። (1ዮሐ. 3:10)

13) ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል።ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ። (1ዮሐ. 3:14-15)

14) እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል።ማንም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል? (1ዮሐ. 3: 16-17)

15) ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።እኛ የእውነት ወገን መሆናችንን በዚህ እናውቃለን (1ዮሐ. 3:18-19)

16) ልባችን የማይፈርድብን ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ድፍረት አለን፤ (1ዮሐ. 3:21)
17) ትእዛዞቹንም የሚጠብቁ ሁሉ በእርሱ ይኖራሉ፤ እርሱም በእነርሱ ይኖራል። በእኛ መኖሩን በዚህ ይኸውም እርሱ በሰጠን መንፈስ እናውቃለን። (1ዮሐ. 3:24)

18) የሚወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተወለደ ነው፤ እግዚአብሔርንም ያውቃል። የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና (1ዮሐ. 4:7-8)

19) መንፈሱን ስለ ሰጠን፣ እኛ በእርሱ እንደምንኖር እርሱም በእኛ እንደሚኖር እናውቃለን። (1ዮሐ. 4:13)

20) ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምኖ በሚመሰክር ሁሉ፣ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። (1ዮሐ. 4:15)

21) በዚህም ዓለም እርሱን እንመስላለንና። (1ዮሐ. 4:17)

22) ማንም፣ “እግዚአብሔርን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና። (1ዮሐ. 4:20)

23) እግዚአብሔርን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደ ምንወድ በዚህ እናውቃለን፤ (1ዮሐ. 5:2)

24) ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። (1ዮሐ. 5:4)

25) ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም። (1ዮሐ. 5:12)

26) ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአት እንደማያደርግ ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚጠብቀው፣ ክፉውም እንደማይነካው እናውቃለን። (1ዮሐ. 5:19)

27) እኛ ከእግዚአብሔር እንደሆንን፣ መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደሆነ እናውቃለን። (1ዮሐ. 5:19)

28) በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ ሁሉ አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን አብም ወልድም አለው። (2ዮሐ. 1:9)

29) ልጆቼ በእውነት [እንደ ክርስቶስ] የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም። (3ዮሐ. 1:4)

30) ነገር ግን መሪ መሆን የሚወደው ዲዮጥራጢስ [leader in the spirit of anti-Christ) አይቀበለንም። ስለዚህ እኔ ከመጣሁ እርሱ በክፉ ቃላት ስማችንን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሁሉ ይፋ አወጣለሁ፤ ይህም አልበቃ ብሎት ወንድሞችን አይቀበልም፤ ሊቀበሏቸው የሚፈልጉትን ይከለክላቸዋል፤ ከቤተ ክርስቲያንም ያስወጣቸዋል። (3ዮሐ.1:9-10)

31) መልካም የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው። ክፉ የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም (3ዮሐ. 1:11)
___
Dr. Girma Bekele
@nazrawi_tube
@nazrawi_tube