Get Mystery Box with random crypto!

​​እንኳን ለጽዮን 'ማርያም ማሕደረ አምላክ' እና ለቅዱሳኑ 'ጐርጐርዮስ ወዮሐንስ' ዓመታዊ በዓል | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​እንኳን ለጽዮን "ማርያም ማሕደረ አምላክ" እና ለቅዱሳኑ "ጐርጐርዮስ ወዮሐንስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

"ጽዮን ማርያም"

"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው:: አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው:: ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም: ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል::

እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በሁዋላ በጊዜው ለእሥራኤላውያን ክብር: ሞገስ: አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል:: (ዘጸ. 31:18) ከዚያም ለ500 ዓመታት ከእነሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች::

ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ: በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ-እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮዽያ መጥታለች:: እነሆ በሃገራችን የ3ሺ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው:: ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን::

ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን:: ግን አንጨነቅም:: ምክንያቱም የመጣችውም: የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም:: በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም:: ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም::

ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን: ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች:: "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው:: "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው::

"ታቦት" ማለት "ማሕደር-ማደሪያ" እንደ ማለት ነው:: ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል:: ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው:: በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም 2 ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን:: (2ቆሮ. 6:16, ራዕይ. 11:19)

#በመጨረሻም_ኅዳር_21 ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን:: በዚህች ቀን:-

1. ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን:: ይሕ ሲሆንም ቅዱስ ሙሴ 40 መዓልት: 40 ሌሊት ጾሞ እንደ ተቀበለ ሳንዘነጋ ማለት ነው:: (ዘጸ. 31:18, ዘዳ. 9:19)

2. በዘመነ ኤሊ ሊቀ ካህናት ታቦተ ጽዮን በታሪኩዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሕዛብ (ኢሎፍላውያን) እጅ ተማርካለች:: ግን ደግሞ ዳጐንን ቀጥቅጣዋለች:: (1ሳሙ. 5:1)

3. በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና: ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ: አገለገለ:: ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ ተቀኘላት:: በዚህም ሜልኮል ንቃው ማሕጸኗ ተዘግቷል:: (1ዜና. 15:25) ሊቃውንትም "ድንግል እመቤታችን ማርያም በትንቢት መነጽር ተመልክቷል" ብለውናል::

"ሰላም ለኪ ማርያም እምነ::
ዘሰመይናኪ ጸወነ::
ሶበ እምርሑቅ ርእየ ዘጽላሎትኪ ስነ::
ለቢሶ ዳዊት ልብሰ ክብር ዘየኀይድ ዓይነ::
ቅድመ ታቦተ ሕግ ኀለየ ወዓዲ ዘፈነ::" እንዲል:: (አርኬ ዘኅዳር 21)

4. በዘመነ ንጉሥ ሰሎሞን (መፍቀሬ ጥበብ) ግሩም የሆነ ቤተ መቅደስ ተሰርቶላት ስትገባ ታላቅ ሐሴት ተደርጉዋል:: እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ንጉሡን አነጋግሯል:: (2ዜና. 5:1, 1ነገ. 8:1)

5. በዚያው ዘመንም በፈጣሪ ፈቃድ ንጉሥ ምኒልክ ቀዳማዊ (ዕብነ ሐኪም) ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮዽያ ገብቷል::

6. በዘመነ አፄ ባዜን (በ4 ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች:: በዚህ ጊዜም 2ቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታል::

7. በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም ነገሥት ጻድቃን አብርሐ ወአጽብሐ 12 መቅደሶች ያሏትን ግሩም ቤተ ክርስቲያን ለእመ ብርሃን ሠርተው በዚሁ ቀን በጌታችን ተቀድሷል::

8. በተጨማሪም በየጊዜው: ማለትም በዮዲት ጉዲትና በግራኝ አማካኝነት ስትፈርስ ወደ ዝዋይ ትሰደድ ነበር:: ተመልሳ ስትታነጽም ቅዳሴ ቤቷ የሚከበረው ኅዳር 21 ቀን ነው:: በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች ይህ በዓል ልዩ ነው::

" አማናዊት ጽዮን እመ ብርሃን ድንግል ማርያምን እንዲህ እንላታለን "

"ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል:: እርሷ "ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት እምቡሩካን: ኅሪት እምኅሩያን" ናትና::

ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች:: እርሷ እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ ናትና::

#እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት: ልዩ" ማለታችን ነው::

1. "ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች ቅዱሳን ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ: ከገቢር: ከኃልዮ ንጽሕት ናት::

"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው: ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: (ተአምረ ማርያም)

2. "ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በሁዋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::

¤ "ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: (ቅዱስ ያሬድ)
¤ ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-ማርያም ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)

3. ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው:: እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::

4. እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና::

#ሼር
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur