Get Mystery Box with random crypto!

​​ኅዳር 20 ቅዱስ አባት አንያኖስ በዚህች ቀን ቅዱስ አባት አንያኖስ አረፈ። እርሱም ለወንጌላዊ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​ኅዳር 20
ቅዱስ አባት አንያኖስ

በዚህች ቀን ቅዱስ አባት አንያኖስ አረፈ። እርሱም ለወንጌላዊ ማርቆስ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ነው።

የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ አረማውያን ናቸው እርሱም ጫማ ሰፊ ነበር ቅዱስ ወንጌላዊ ማርቆስም ወደ እስክንድርያ አገር መጀመሪያ በገባ ጊዜ እግሩን ተደናቅፎ ጫማው ተቆረጠ እንዲሰፋለትም ወደ ጫማ ሰፊ አንያኖስ ዘንድ ሔደና ጫማውን ሰጠው መስፋትም በጀመረ ጊዜ መስፊያው ጣቱን ወጋው በዮናኒም ቋንቋ አታኦስ አለ ትርጓሜውም አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው። ቅዱስ ማርቆስም የእግዚአብሔርን ስም ሲጠራ በሰማ ጊዜ ደስ ብሎት የክብር ባለቤት ክርስቶስን አመሰገነው።

ከዚህም በኋላ አፈር አንሥቶ በምራቁ ጭቃ አድርጎ በአንያኖስ ጣት ላይ አደረገውና በዚያን ጊዜ አዳነው አንያኖስም ከዚህ ድንቅ ምልክት የተነሣ አደነቀ ቅዱስ ማርቆስንም ወደ ቤቱ ወሰደው ስለ ሥራው ስለ አምልኮቱም የመጣውም ከወዴት ቦታ እንደሆነ ጠየቀው።

ቅዱስ ማርቆስም ከብሉያትና ከሐዲሳት መጻሕፍት የአንድ እግዚአብሔርን ህልውና ስለ ዓለሙ ሁሉ ድኅነት የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን፣ መከራ መስቀልንም ተቀብሎ ስለመሞቱ፣ ስለ ትንሣኤውና፣ ስለዕርገቱ፣ ዳግመኛም ለፍርድ ስለ መምጣቱ ይነግረው ጀመረ።

የአንያኖስም ልቡ ብሩህ ሆኖለት በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ከቤተሰቡ ሁሉ ጋር ተጠመቀ። የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ በላያቸው ወረደ አዘውትሮ በመጠመድ የሐዋርያ ቅዱስ ማርቆስን ትምህርት የሚሰማ ሆነ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሕጓንና ሥርዓቷንም ተማረ።

ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሌሎች አገሮች ሒዶ ለማስተማር በፈለገ ጊዜ እጆቹን በአንያኖስ ላይ ጭኖ በግብጽ አገር ለወገኖቹ ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ሊቀ ጵጵስና ሾመው እርሱም ብዙዎችን አስተምሮ አጠመቃቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ቤቱንም ቤተ ክርስቲያን አደረጋት እርሷም በስተምዕራብ ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ያለች ዛሬ የሰማዕት ቅዱስ ሰርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሁና የታወቀች ናት።

ይህ የተመሰገነ አባት አንያኖስም በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሼር አድርጉ
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur