Get Mystery Box with random crypto!

የተሰጠንን ተልዕኮ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን ሰላም እናረጋግጣለን ፦ ሌተናል ጄኔራል ዘ | Natnael Mekonnen

የተሰጠንን ተልዕኮ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን ሰላም እናረጋግጣለን ፦ ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ

አዛዡ የአሃዱዎችን የግዳጅ አፈፃፀም በተመለከተ ከሠራዊት አባላቱ ጋር የተወያዩ ሲሆን ማዕከላዊ እዝ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና አሸባሪውን የሸኔ ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጥፋት ቡድኑ የሚንቀሳቀስባቸው ዞኖች ወደ ሰላምና ልማት እንዲመለሱ በማድረግ ተልዕኳችንን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

ዕዙ የሠራዊቱን የማድረግ አቅም የሚያጎለብቱ ስልጠናዎችን ከግዳጅ ጎን ለጎን በመስጠት የአመራሩንና የአባሉን ስነ ልቦናዊ፣ አካላዊና ታክቲካዊ ክህሎቱን በማሳደግ ግዳጁን በብቃት የሚፈፅም ሰራዊት ገንብተናል ፤ ሰራዊቱ ማንኛውንም ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ መሰናክል በማለፍ ጠላትን መደምሰስ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል ሲሉም ገልፀዋል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበል ጫካ የመረጡ ሀይሎች በራሳቸው ጊዜ የቀረበላቸውን አማራጭ እንዲቀበሉ ካልሆነም ተበትኖ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የሸኔን የሽብር ቡድን በመደምሰስ አስፈላጊውን ዋጋ ከፍለን ሰላምን ለህብረተሰቡ እናረጋግጣለን ሲሉ ጄኔራል መኮንኑ ተናግረዋል።

ከሠራዊቱ ጋር ፊት ለፊት የተወያዩት ሌተናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ የቀጣይ ተልዕኮ ውጤታማነት የሚረጋገጠው የሰራዊቱ ሞራላዊና ስነ- ልቦናዊ ዝግጁነት የተገነባ ሲሆን መሆኑን ጠቁመው እስካሁን በስልጠና ላይ የተፈጠሩ አቅሞች ይህንን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ማዕከላዊ ዕዝ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ከህብረተሰቡና ከፀጥታ ሀይሉ በመጣመር ሰላም በማረጋገጥ ለህዝቡ እፎይታ ለመስጠት የተለመደ ጀግንነቱን እና ድል አድራጊነቱን ለማስቀጠል መነሳሳት ይገባል ሲሉ ለሰራዊቱ አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል።