Get Mystery Box with random crypto!

ወጣት ሶፎኒያስ አስራትን ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ወንጀል ፈፃሚ | Natnael Mekonnen

ወጣት ሶፎኒያስ አስራትን ገድለው ተሽከርካሪውን ዘርፈው የተሰወሩ ማንነታቸው ያልታወቁ ወንጀል ፈፃሚዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ከዘረፉት ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ወንጀሉን የፈፀሙ አካላትን ለመቆጣጠር የምርመራና የክትትል ቡድኑ ሌት ከቀን በመስራት ውጤት ማምጣቱ ገልፆል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ወደ አቦ ቤተ-ክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ ወጣት ሶፎኒያስ አስራት ተገድሎ ይገኛል፡፡

የወጣቱ መገደል ሪፖርት የደረሰው አዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራና የክትትል ቡድኖችን በማዋቀር የገዳዮቹን ማንነት በማወቅ ወንጀለኞቹን ህግ ፊት ለማቅረብ ወደ ስራ ይገባል፡፡
ሟች ወጣት ሶፎኒያስ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ/ም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ናሆም ሆቴል አካባቢ ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸው የማይታወቁ ሦስት ግለሰቦችን አሳፍሮ ወደ ቦሌ ሚካኤል ለማድርስ መሄዱን ጉዳዩን ለመከታተል የተቋቋመው የምርመራና የክትትል ቡድን አባላት ባደረጉት ክትትል ያረጋግጣሉ፡፡
ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወንጀል ለመፈፀም አቅደው እና ተደራጅተው የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ መስለው ሹፌሩን በመቅረብ ከተሳፈሩ በኋላ አንገቱን በገመድ አንቀው በመግደል አስክሬኑን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ወደ አቦ ቤተክርስቲያን በሚወስደው መንገድ ላይ በመጣል አይነቷ ቪትዝ የሴሌዳ ቁጥር ኮድ 2A 93488 ተሽከርካሪ ጨምሮ ሁለት ሞባይል ስልኮችን ዘርፈው ይሰወራሉ፡፡

ፖሊስ ሌት ተቀን ባደረገው ብርቱ ክትትል ልዩ ልዩ ፖሊሳዊ ቴክኒኮችን በመጠቀም ወንጀል ፈፃሚዎቹ የሰረቁትን ተሽከርካሪ ለመሸጥ እየተስማሙ መሆኑን በበቂ ማስረጃ ካረጋገጠ በሗላ ክትትሉን በመቀጠል ሦስቱን ዋና ወንጀል ፈፃሚዎች የሰረቁትን መኪና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ለመሸጥ እየተደራደሩ እንዳለ በቁጥጥር ስር በማዋል የተሰረቀችውን መኪና ፣ ሁለት ሞባይል ስልኮችን ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶችን ይዞ ምርመራውን መቀጠሉን ጨምሮ ገልፆል፡፡ ፖሊስ ባደረገው ክትትልና ምርመራ ማንነታቸው የማይታወቁ ወንጀል ፈፃሚዎችን በ48 ሰዓት ጊዜ ውስጥ በመለየት ሦስት ዋና ወንጀል ፈፃሚዎችንና ሦስት ግብራበሮቻቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ታውቋል፡፡

በመጨረሻም ለዚህ ስራ ስኬታማነት ቀና ትብብር ላደረጉ አካላት አዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋናውን እያቀረበ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የጥሪ ማዕከል ቁጥሮችን ሳይጠቀሙ አገልግሎት መስጠት ሆነ መቀበል እንዲሁም ከሚታወቀው የአገልግሎት አሰጣጥ ውጭ በዋጋ ድርድር የሚሰጥ የትራንስፖርት ግልጋሎት ለእንዲህ አይነት ወንጀል እየዳረገ ስለሆነ ተሳፋሪዎች ሆኑ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡የምርመራ ሥራው እንዳበቃ የፍርድ ሂደት ውጤቱን በቀጣይ ለህዝብ እንደሚገለፅ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል ፡፡