2022-08-30 20:44:36
የተከፈተብንን ዘርፈ ብዙ ጦርነት ሁሉም ዜጋ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት መመከት አለበት – ዶ/ር ለገሰ ቱሉ
የውስጥ ባንዳዎችና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተቀናጅተው የከፈቱብንን ዘርፈ ብዙ ጦርነት ሁሉም ዜጋ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት መመከት አለበት ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለፁ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ባንዳዎቹ በአፈቀላጤዎቻቸው በአንድ በኩል “ጦርነቱ አንተን አይመለከትም” እያሉ ይገዘታሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሂሳብ እናወራርደለን፣ ኢትዮጵያን ለማፍራስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን እንደሚሉ ጠቁመዋል።
“ከአማራ ህዝብ ጋር ፀብ የለንም እያሉ የአማራን ሴቶችና ሕጻናት ይደፍራሉ፣ ንብረቶቻቸውን ይዘርፋሉ፣ በአደባባይ ያዋርዳሉ፣ መሰረተ ልማቶቻቸውን ያወደማሉ” ነው ያሉት።
በተመሳሳይ የአፋር ህዝብ እየታገለም፣ ንብረቱ እየወደመበትም፣ ራሱ እየተራበም ቢሆን ለትግራይ ወንድሞቹ ሰብአዊ እርደታ ሳይስተጓጓል እንዲቀርብ እያደረገ ከቀዬው እንዲፈናቀል፣ የዘር ፍጅት እንዲደርስበት ማድረጋቸውን አስደርተዋል።
ኦሮሞው፣ ሶማሌው፣ ጉሙዙ ወዘተ ወዳጆቻችንና አጋሮቻችን ናቸው እያሉ ከቅጥረኛ ሽብርተኞችና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ተቀናጅተው እርስ በርስ እንዲፋጁ፣ መሰረተ-ልማቶቻቸው እንድወደም፣ ሃብት ንብረታቸው እንዲዘረፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
ለመሆኑ ይህ እኩይ ድርጊታቸው የቅድስና ስራ ነው እንዴ? ሲሉ የጠየቁት ሚኒስትሩ፥ ሰብአዊ እርዳታን እንደመሳሪያ ተጠቅመው በኋላ ቀር የጦርነት ስልት የትግራይን ህጻናት፣ አዛውንቶችና ሴቶችን ሲማግዱ ምነው የኢትዮጵያ ወጣት ወደ ጦርነት አትግባ ብለው የራራው አንጀታቸው ለትግራይ ሲሆን ምነው ጠነከረ? ሲሉም ጠይቀዋል።
የህወሓት መሪዎች እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ ምቾት እና ድሎታቸው አይጓደል እንጂ የትግራይ ህዝብ እና ወጣት እንደአቧራ ቢቦኑ፣ እንደጉም ቢተኑ፣ እንደ ቅጠል ቢረግፉ ለቅፅበትም ያህል አይገዳቸውም ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ህዝብ የሚያመጣው አንዳችም ተስፋ እንደሌለ ሚኒስተሩ ተናግረዋል።
በትግራይ ህዝብ ስም ተለምኖ የመጣን የዕርዳታ ስንዴ እና ነዳጅ በመስረቅ ለጦርነት መጠቀም የኖረበት የቡድኑ አስነዋሪ ገፅታ እንደሆነ በማወቅ የትግራይ ወጣት ቡድኑን በማውገዝ ሞት እና ስደት እንዲቆም የጋራ ድምፁን ሊያሰማ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ህዝባችን ሆይ ንቃ ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሀገር በጦርነት ውስጥ ሆና ገለልተኛ ነኝ ብሎ መቀመጥ ከአንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ እንደማይጠበቅ አመልክተዋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው አቅም ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ፈርጀ ብዙ ጦርነት መመከት በማለት፥ በጦር ግንባር፤ በደጀንነት፤ በሳይበር ውጊያ እና በሌሎችም መንገዶች ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት በጋራ መቆም የህልውና ግዴታ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
“ሀገር ሁሉም ነገር ናት! ሀገር መኖሪያ ናት፤ ሀገር እኛነታችን የተገነባባት እሴት ናት፤ ሀገር አብሮ በሚኖር በምንወደው በምናከብረው ህዝብ ትገለጻለች፤ ሀገር የልጅ ልጆቻችን የሚረከቧት የትናንት ታሪካችን፤ የዛሬ ሀብታችን እና የነገ ተስፋችን ናት” ብለዋል።
እኛነታችንን የቀረፀች፣ መኖሪያችን የሆነች እና የነገ ተስፋችንን የሰነቀች ሀገራችን እንድትጠፋ በተለያዩ መስኮች ጦርነት ተከፍቶባታል ያሉት ዶክተር ለገሰ፥ እኛነታችን የሆነችው ኢትዮጵያችን እንደ ጠላት ፍላጎት እንዳትጠፋ ሁላችንም ከመንግስት ጎን በመሆን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሠራዊታችን ጀግንነት መገለጫው፤ ድል መዳረሻው፤ ህዝባዊነት ስንቁ የሆነ የኢትዮጵያ ጀግና፤ ፅኑ ዘብ መሆኑንም ገልፀዋል።
በማንኛውም ጊዜ እና ሁኔታ ለመከላከያ ሰራዊታችን ያለንን ክብር ያለስስት ማሳየት አለብን ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከምንም በላይ ውድ የሆነውን ህይወቱን ለሚሰጠን ጀግናው ሰራዊታችን ደጀንነታችንን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ልናሳየው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሰራዊታችን የሀገሩን ረሀቧን እየተራበ፤ ጥሟን እየተጠማ፤ መከራዋን እየተሸከመ ኢትዮጵያን እየጠበቀ ያለ ብሔራዊ ክብራችን እና ሀብታችን ነው ብለዋል፡፡
1.3K views17:44