2022-06-29 07:20:13
#ጩኸት____ሲበረክት...
ስለምን እንሸበራለን ለምንስ እንደበቃለን
"መንጋ" የሚሉ መንጋዎችና በተቃራኒ የቆሙ ቢጤዎቻቸው ሲጯጯሁ የኛ ህልውናና እጣ ፈንታ በነሱ ላይ ብቻ የተወሰነ ለምን ይመስለናል
ከመጮህና ከጨለማ ውጪ አማራጭ የሌለ ለምን ይመስለናል
ተስፋ የተባለው ውድና እንቁ ሀብት እንዴት በኳኳታ የሚረታ መሰለን እንዴትስ ሰው የሚለውን ውድና ጠንካራ ማንነታችን በዚህችና በነዚህች ለመገደብና ለመበየን ደፈርን ጩኸት ሲበረክት አለመስማት ካልቻልን እናጠይቀዋለን እንጂ አንረታም። ባይሆን ጩኸት የማንደግምና የማናስተጋባ ራስነታችንን ይዘን መገለጥና መቆም ከሰውነታችን ይጠበቃል። ከዙሪያችንም ከሰውነታችንም ችግሮቹ የራቁ አይደሉም። ከወለጋ ጫካ ባልተናነሰ በትልቋ ኢትዮጵያ ካባ ስር ያደፈጥን የበለጠ እናሰጋለን። ርቀን ሳንሄድ የዙሪያችንን ጉድፍና ገዳይ እንይ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለመፍትሄው ባለንና በሚልቀው እልፍ ተስፋና ሰውነታችን ላይ እንቁም። በሰውነት እንገለጥ። እኔ ዛሬ ከገደሉን በባሰ ሀሳብና ተስፋን ሲገድሉ የከረሙትንና የሚገድሉትን የበለጠ አስታውሳቸዋለው። የገዳዮቹን ቃል አቀባዮችና ጉልበት የሆኗቸው የዙሪያዬን ሞት ሸቃጮች በጉልህ አውቃቸዋለሁ። ጩኸትና ግፍን ባንዲራ ብናለብሰው፣ በዜማ ብናጅበው፣ በማይክ ብናንቆረቁረው፣ በብሄር ብብት ውስጥ ብንወሽቀው ያው ድንቁርና ነው። መጠሪያው ገዳይነት ነው። ግፈኝነት! የዛሬ ወይም የነገም ገዳይና አስገዳይነት!
የወገንን ሲቃና ጣር፣ እንዲሁም ተስፋ ጭምር እንዴት "ጩኸትና ጨለማ" በሚሏቸው አሁናዊ ተራ መሸቀጫዎች መሸፈንና ማሸነፍ ይታሰባል ይህ ለሰውነታችንም ለእውነታውም ፍፁም የራቀ ነው። ተስፋ ማድረግ የትግሉም፣ የሰውነትም ዋነኛው ክንድ ነው። ብሩህ የሆነው ሁሉ እንዲመጣ ከጩኸቱ ገዝፈን እንታይ። ለብርሀኑ እናዋጣ። ካልቻልን ግን ስለነሱ ጩኸት አንሸማቀቅ። እኔ ለወገኔ ብሩህና ብሩህ ዘመን እንዲመጣ ጨለማው ከማይመስጣቸውና ጨለማ ከማያዋጡት አንዱ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ብሩህ ቀን ለሁላችን
450 views04:20