Get Mystery Box with random crypto!

ከአማራ ክልል በተለይ ከሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ወደ አ/አ በሚገቡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያ | Mereja today news

ከአማራ ክልል በተለይ ከሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎች ወደ አ/አ በሚገቡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው መንገላታት አሁንም ዘላቂ መፍትሄ እንዳላገኘ የቲክቫህ ቤተሰብ አባላት አሳውቀዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ከተለከው ጥቆማ በተጨማሪ ሰሞኑን በስራ ፈተና፣ ለትምህርት ጉዳይ እና ለህክምና ወደ አ/አ መግባት የነበረባቸው ወገኖች ወደ ኃላ እንዲመለሱ ተደርገዋል።

አንድ የቤተሰባችን አባል ከእህቱ ጋር (ለእህቱ ህክምና) መናሻውን ኮምቦልቻ አድርጎ ወደ አ/አ ጉዞ እያደረገ ነበር ሸኖ ላይ የአዲስ አበባ/የኦሮሚያ መታወቂያ ከሌላችሁ አትገቡም በመባለቸው ወደ ኮንቦልቻ ተመልሰው በፕሌን ለመሄድ መገደዳቸውን ገልጿል።

" እባካችሁ መሪ ካለን ይምራን እኛ ምን አደረግን ይሄ ነገር ደግሞ የሁለቱን ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርን ይመለከታል " ሲል ቅሬታውን አቅርቧል።

በተጨማሪ ትላንት ከደሴ ወደ አ/አ እየመጣ የነበረ የቤተሰባችን አባል ጫጫ ላይ የአ/አ መታወቂያ ስላለው ማለፉን ነገር ግን እዛው የቀሩ ሴቶች፣ አዛውንቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እንደነበሩ አመልክቷል።

የፌዴራል መንግስት ኮሚኒኬሽን ከቀናት በፊት ለቪኦኤ በሰጠው ቃል ጥብቅ ቁጥጥርና ፍተሻ እየተደረገ ያለው በተለይ አዲስ አበባ ላይ የተቃጣ የጥፋት እቅድ (በህወሓትና ሸኔ) መኖሩ ለደህንነት አከላት መረጃ በመድረሱ መሆኑን ገልጿል። በዚህ ሳቢያ በዜጎች ላይ እንግልት እያጋጠመ እንደሆነ አልሸሸገም።

በፀጥታ አካላት በኩል የፍተሻ አፈፃፀም ለዜጎች ምሬት ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ የደህንነት ስራው አፈፃፀም ላይ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት፤ በተጨማሪ የደህንነትና የፀጥታ መዋቅሩን ማጥራት እንደሚገባ ታምኖበት እየተሰራ ነው ብሏል። በዋነኝነት ግን ስራው የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበት ውጭ ሌላ ዓላማ እንደሌለው ገልጿል።