ዖዝያን.... በክብር ቢቀባ ፥በአስራ ሶስት አመቱ፤ በዙፋን ቢቀመጥ፥ ፀንቶለት ሹመቱ። እግዚአብሔር | መንፈሳዊ ግጥሞች ዘ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ዖዝያን....
በክብር ቢቀባ ፥በአስራ ሶስት አመቱ፤
በዙፋን ቢቀመጥ፥ ፀንቶለት ሹመቱ።
እግዚአብሔር ነገሩን፥ እየከወነለት፣
እልፍ እየማረከ፥ እልፍ ቢያስገዛለት።
፡
በበረታ ጊዜ፥ ለጥፋት ታበየ፤
በመቅደሱ ሊያጥን፥ ጽና ይዞ ታየ።
ካህኑ የአሮን ልጅ፥ ዓዛርያስ ሳለ፤
ንግስናውን ትቶ፥ ንጉስ ልጠን አለ።
፥
የእግዚአብሄር ፍርድ፥አይለወጥምና ፤
ተመለስ ንጉስ ሆይ፥ በዙፋንህ ጽና፤
ጽና ይዞ ማጠን፥ ያንተ አይደለምና፤
ቢለው አልሰማ አለ፥ ካህኑን ናቀና።
፥
የትዕቢቱ መጠን፥ ዙፋኑን ነቀነቆ፤
ለየው ከንግስና፥ ካባውን አውልቆ።
ያደረገለትን ሀይል፥ ክብሩን ዘንግቶ፤
ንጉስ ልጠን አለ፥ ቤተመቅደስ ገብቶ።
፥
እግዚአብሄር ቀሰፈው፣ ለምጽን አተመበት፤
በቤተ መንግስቱ፥ ልጁ ነገሰበት።
የማይነካ ነክቶ፥ንግስናው ተሻረ፤
ከአባቶቹ ርቆ፥ በእርሻ ተቀበረ።
፥
ዛሬም ዖዝያን ሆይ!
በበረታህ ጊዜ፥ ጌታህን አትርሳ፤
እርሱ ነው የሚሰጥ፥ እርሱ ነው ሚነሳ።
ካህኑን አትንካ፥ የጌታን አገልጋይ፤
ቁልፍ አለና በእጁ፥ የመንግስተ ሰማይ።
++++
አንድ ቤተክርስቲያን
አንድ ሲኖዶስ
አንድ ፓትሪያርክ
አንድ መንበር
+++++
ሰማይ ስማ፥ ምድር አድምጪ፤
ቀን ወጣልኝ ብለሽ፥ ከሕጉ እንዳትወጪ።
በበደል ላይ በደል፥ እየጨመራችሁ፤
ዖዝያኖች ዛሬም፥ ትቀሰፋላችሁ።
++++++
ታዜና
#መንፈሳዊ_ግጥሞች
t.me/Menfesawigetmoch