Get Mystery Box with random crypto!

የዘር ፖለቲካ እምነታችንን እንዳይነጥቀን ~ ከ150 አመታት በፊት የኩሽ ህዝብ እምነት ዋቄፈና ነበ | Bilal Media & Communication

የዘር ፖለቲካ እምነታችንን እንዳይነጥቀን
~
ከ150 አመታት በፊት የኩሽ ህዝብ እምነት ዋቄፈና ነበር የሚል ፅሁፍ አየሁኝ። ይሄ ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው። በኩሽ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦች ውስጥ ሶማሊና አፋር ይጠቀሳሉ። የሁለቱም ህዝቦች እስልምና የ150 አመት ታሪክ አይደለም።
ምናልባት ፀሀፊው ኩሽ ሲል የሚፈልገው ኦሮሞ ማለቱ ይመስላል። ፍላጎቱ እንደዚያ ከሆነም፡
1- ኩሽ በሚል ሌሎች ህዝቦችን በሚጠቀልል ሰፊ ቃል መግለፁ ተገቢ አይደለም።
2- የኦሮሞ ህዝብም ቢሆን የእስልምና ታሪኩ የመቶ አምሳ አመት ታሪክ አይደለም፤ በተለይም የምስራቁ ክፍል።

ለፖለቲካዊ ግብ ሲባል የኦሮሞን ህዝብ ከኢስላም የማራቅ ጥረቶች በተደጋጋሚ ይታያሉ። "እስልምናም ክርስትናም መጤ ናቸው፤ ነባሩ እምነታችን ዋቄፈና ነው"፣ "ሃይማኖት ህዝባችንን ለያይቷል" ፣ ... በሚሉ ሴራዎች ሙስሊሙ ለሃይማኖቱ ጀርባ እንዲሰጥ ለማድረግ የሚሞክሩት ቀላል አይደሉም። ቁጥሩን መገመት ባይቻልም በነዚህ አካላት ወጥመድ ውስጥ የወደቁ ሙስሊሞች በተጨባጭ አሉ። "ኦሮሞነት ከሃይማኖትም በላይ ነው" የሚሉ ሰዎችን ማየት በጣም የሚዘገንን ነገር ነው።
ወገኔ ዘር፣ ጎሳ፣ ብሄር፣ ... እንደ ኢስላም ተራ ነገሮች ናቸው። ኢስላም ከዘር፣ ከሃገር ቀርቶ ከህይወትም በላይ ነው። ከሃገርም ከዘርም በላይ ስለሆነም ነው ሶሐቦች አገራቸውን ጥለው ሐበሻ ድረስ የተሰደዱት። ስለሆነም ነው ነብያችን ሶላለሁ ዐለይሂ ወሰለም መካን ያክል አገር ጥለው የተሰደዱት። ኢስላም ከዘር በላይ ስለሆነም ነው ሶሐቦች በበድርና በኡሑድ ዘመቻ ቁረይሾች ጋር በሰይፍ የተሞሻለቁት። ከኢስላም የሚበልጥ ቀርቶ የሚወዳደር እንኳ ምንም ነገር የለም። ስለ እምነቴ አንገቴን እሰጣለሁ። ስለ ብሄሬ ግን ጠብታ ደም አልገብርም። ለብሄሬ ስል የማንንም ነፍስ ቀርቶ ጠብታ ደም አላፈስም። ብሄርን ብቻ ነጥሎ መሰረት ላደረገ ትግል የስሙኒ አስተዋፅኦ እንዲኖረኝ አልፈልግም።
ወላጆቼ፣ ቤተሰቦቼ ከዘር ማንነት ከቋንቋ በላይ ናቸው። ኢስላሜ ደግሞ ከነሱም በላይ ነው። በዘርም በጉርብትናም የማልቀርበው የጉራጌ ሙስሊም (ምሳሌ ነው) በዘር ከሚገናኘኝ ሙስሊም ያልሆነ ጎረቤቴ በላይ ለልቤ የቀረበ ነው። ኧረ ፈፅሞ ለንፅፅርም አይቀርቡም።
መጠቆም የፈለግኩት የዘር አጀንዳ ከልክ አልፎ እምነታችንን በሚነጥቅ ደረጃ ስለ ደረሰ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ዱዓቶችና መሻይኾች ሳይቀሩ የችግሩ ሰለባ እየሆኑ ስለሆነ ከፍተኛ የማንቃት ስራ ያስፈልጋል። በዘር ሰበብ ባሳዛኝ ሁኔታ የሙስሊም ደም በያካባቢው እየፈሰሰ፣ ሚሊዮኖች እየተፈናቀሉ በርካታ መሻይኾችና ታዋቂ ሰዎች "አላህን እንፍራ" የሚል ማስታወሻ ለማስተላለፍ እንኳ ወኔ አጥተዋል። ያሳዝናል።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor