Get Mystery Box with random crypto!

የእመቤታችን ለቅሶ ልመናዋ ክብሯ ለዘላለሙ ከእኛ ጋር ይኑርና ፤ አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወል | የአህዛብና የመናፍቃን ጥያቄዎችና መልሶቻቸው!!

የእመቤታችን ለቅሶ

ልመናዋ ክብሯ ለዘላለሙ ከእኛ ጋር ይኑርና ፤ አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኖ የብህንሳ ኤጲስ ቆጶስ አባ ሕርያቆስ ድንግል ማርያም እመቤታችን ስላለቀሰችው ልቅሶ በዛሬው ቀን የደረሰው ይህ ነው አሜን።

ወደ ዮሐንስ ቤትም በደረሰች ጊዜ አልዘገየችም ወደቀራንዮ ተመልሳ ልትሄድ የተወዳጅ ልጅዋን የመከራውን ፍጻሜ ታይ ዘንድ ቸኮለች እንጂ። በመስቀል ላይ ነፍሱን በፈቃዱ ሰጥቶ ዝም በአለ ጊዜ በምድር ላይ ስለሆነው ንውጽውጽውታና በሰማይም ስለተደረጉ አስደናቂ ተአምራቶች ሀገሪቱ ሁሉ ተሸበረች ፤ ድንግል እመቤታችንም ምድር ስትናወጽ ጨለማም በምድር ሁሉ ስትሰለጥን አይታ እነሆ እነዚህ ተአምራቶች የልጄ የሞቱ ምልክቶች ናቸው ብላ ጮኸች።

እንዲህ ስትልም ዳግመኛ ዮሐንስ ደርሶ
እያለቀሰ ከእርሷ ዘንድ ቆመ።
ድንግል እመቤታችንም ዮሐንስ ሆይ በመስቀል ላይ ልጄ በእውነት ሞተን? አለችው።እርሱም ራሱን ዝቅ አድርጎ እናቴ ሆይ አዎን ሞተ አላት።

ከዚህም በኋላ ታላቅ ልቅሶ ሆነ በዚያችም ሰዓት ድንግል እመቤታችንን ፍጹም ጩኸትና ልቅሶ ጸናባት ፤ በመረረ ልቅሶም እየጮኸች ልጄ ሆይ ከዚህ ካገኘህ የሞት ፃዕር የተነሣ ግፌን የሚመለከትልኝ ሹም ወይም በሐዘን የተሰበረውን ልቤን አይቶ በማስተዋል የሚፈርድልኝ ዳኛ አላገኘሁም አለች። መኮንን ሆይ እንደ ሕጉ የምትፈርድስ ቢሆን ኖሮ ንጉሥ ልጄን እንደራበው እንደጠማው የአይሁድ ወገኖች ባልሰቀሉትም ነበር።

አንተም ሊቀ ካህናት በዕውነት ፈራጅ ብትሆን ባርያ በጌታው ፈንታ መሞት በተገባው ነበር።ቨሹም ሆይ በቅን የምትፈርድ ብትሆን ልጄን በበርባን ፈንታ ባልሰቀልከውም ነበር። አንተም ሊቀ ካህናት በዕውነት የምትፈርድ ብትሆን ከልጄ ይልቅ ይሁዳ ለሞት የተገባ በሆነ ነበር።

ሹም ሆይ ፍርድን የምታውቅ ቢሆን ልጄን ሥጋውን አራቁተህ መስቀል ባልተገባህም ነበር። ሊቀ ካህናት ሆይ በቅን የምትፈርድ ብትሆን ወንበዴውን አድነህ ጻድቁን ባልገደልከውም ነበር።
ዳኛ ሆይ መልካም ፍርድን የምታውቅ ብትሆን ኑሮ ጦሮች በላይህ ላይ ሲያንጃንብቡ ጽኑዕ የሆነውን ባልገደልከውም ነበር። አንተም ሊቀ ካህናት በቅን የምትፈርድ ብትሆን የጌታህን ፊት ባፈርክ ነበር።

እኔ ስለጦርነት ሰልፍ ስሰማ የንጉሥ ልጅ በጦርነቱ ውስጥ የተያዘ እንደሆነ እንዳይሞት ስለእርሱ እጅግ በርትተው እየተዋጉ ወደ አባቱ በፍጹም ጌትነትና ክብር እስከ አደረሱት ድረስ ይጠብቁታል።

ሊቀ ካህናት ሆይ ለምን እንዲህ ሆነ ብለህ በጠየቅኸው ጊዜ ዕውነቱን አስረዳህ ፤ ግን በአንተ ዘንድ የተጠላ ሆነ። ሐሰትን ወደድክ ፤ እምነትህንም በሐሰቱ ላይ አጸናህ ፤ እንግዲህ ከእውነተኛው ከእርሱ በስተቀር ማንን ትጠይቃለህ።

በፊትህ የቆመው እርሱ እውነተኛ እንደሆነ አታውቅምን? እርሱም በእውነት ሕይወት ነው።

ንጽሕት ድንግል ሆይ በኢየሩሳሌም ከተማ በዚህ ትውልድ መካከል የሆነውን ታላቅ ግፍ እዪ ፤ እነሆ ከእነርሱ በሚበልጠው ላይ ተሰብስበው ለሞት ፍርድ ሰጥተውታልና። ከዚህ ሁሉ በኋላ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደሆነ ነበር ፤ የመቶ አለቃውም በዕውነት ይህ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ አመነ ፤ እሊህ ተአምራቶቹ በሁሉ ዘንድ ታመኑ።
በዕንጨት መስቀል ላይ ሳለ ምእመናን ሁሉ በአንድነት አለቀሱለት።

ስለ ጌታ ስቅለት ከሄሮድስ ዘንድ ወደ መጣው የመቶ አለቃ ጲላጦስ ልኮ አስመጥቶ ወደ ቤቱ አስገብቶ ወንድሜ ሆይ ይህን ጻድቅ ሰው አይሁድና ሄሮድስ ያደረጉትን አየህን? ይህ ሁሉ ተአምራት በምድር እስኪሆን ድረስ በግፍ ሰቀሉት።
ወንድሜ ሆይ በእውነት እነግርሃለሁ ፤ እነዚህ ክፋቶች ሁሉ የተፈጸሙት በሄሮድስ ምክር እንጂ በእኔ ፈቃድ አይደለም ፤ እኔ እንዳይሞት ልተወው ወደድኩ ፤ ነገር ግን ሄሮድስ በዚህ ደስ እንደማይለው ባየሁ ጊዜ ይሰቅሉት ዘንድ ለአይሁድ ሰጠኋቸው እንጂ።

ተመልከት አሁን ለእግዚአብሔር ስለሰቀልነው ልጁ ምን ብድርን እንከፍለዋለን? አለው ፤ የመቶ አለቃውና ባለጦሩ ከጲላጦስ ጋር ደሙ በሄሮድስና በካህናት አለቆች ላይ ነው እያሉ መራራ ልቅሶ አለቀሱ። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ ልኮ የካህናት አለቆች ቀያፋና ሐናን ወደ ጉባዔው አስጠርቶ እናንተ በግፍ ደምን የምትጠጡ ተኵላዎችና ቀበሮዎች በዕንጨት መስቀል ላይ ወደሞተው የናዝሬት ሰው አሁን ተመልከቱ ደሙም በእናንተና በልጆቻችሁ ላይ ይሁን አላቸው።

እነርሱ ግን ደስ በመሰኘት እያፌዙ ደረታቸውን እየደቁ ፊታቸውንም እየነጩ እስከ ሽህ ትውልድ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። ጲላጦስም ይህ ሁሉ ተአምር በሰማይና በምድር ከተገለጠ በኋላ ዛሬም ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አትፈሩምን? ፣ አትደነግጡምን? አላቸው።

እነርሱም እንደ ሕጋችን ፈጽመናል ስለምን እንፈራለን? እንደነግጣለን? አሉት።
ጲላጦስም የሐሰት ሕግ ፈጸማችሁ እንጂ ይህ ሕግ አይደለም አለ ፤ አንተም ሊቀ ካህናት የተባልከው እነሆ ልብሶችህ ተቀደዋል። ሕጉም ሊቀ ካህናቱ ልብሶቹን በቀደደ ጊዜ ከክህነት አገልግሎት ይከልከል ይላል።

ቀያፋም እኔ ልብሴን የቀደድኩት እርሱ በእግዚአብሔርና በሕጋችን ላይ የስድብ ቃል ስለተናገረ ነው ብሎ መለሰለት።
ጲላጦስ እንግዲህ በሊቅ ካህናት ሥርዓት ወደ መቅደስ እንድትገባ አልፈቅድልህም እንደ ሕግ አፍራሽ እንጂ። አንተ ወደ መቅደስ እንደገባህ ሌላው ቢነግረኝ ቸብቸቦህን ከአንተ ላይ እቆርጣለሁ አለው።

ቀያፋም ከአንተ በፊት ብዙ ጊዜ አልፎአል ፤ ብዙዎች ሹማምንት የሚቀድሙህ አሉ እስከ ዛሬ የካህናት አለቆችን ወደ መቅደስ መግባትን የከለከላቸው አለን? ብሎ መለሰለት። ይህንም ያለ የሄሮድስን ሥልጣን በመተማመን ነበር ፤ ጲላጦስም ይህን ሁሉ ተአምር ስታይ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አሁንም ልብህ አያምንምን? አለው።

ሊቀ ካህናት የተባለ ቀያፋም አንተስ በዚች አገር አዲስ ተክል ነህ ይህ ምልክት የሆነበትን ነገርና የተደረገውን አታውቅም። ይህ ይቅርታ የሚደረግበት የመጋቢት ወር ፀሐይና ጨረቃ ዑደታቸውን ፈጽመው ተራክቦ የሚያደርጉበት ሲሆን በዚሁ ወር መሠርያኖች ጨረቃን እንደ ደም የሚሆንበትን ያደርጋሉ ፤ የፀሐይንም ብርሃን በሥራይ ኃይል ይስባሉ።
የአግዓዝያንንም ተግባር ይመርምራሉ ፤ የስንዴውን የወይንንና የዘይትን ፍሬዎች በማዘጋጀት ይህን የመሰለውን ቀያፋ በሐሰት ይናገር ነበር።

ጲላጦስም ከወንበሩ ላይ ተነስቶ አንተ እርሱን ከመጥላትህ የተነሣ በዓለሙ ሁሉ ላይ መዐትን ልታመጣ ትወዳለህ? ብሎ ከቆዳ በተሠራ በደረቀ በትር ደበደበው ፤ ጽሕሙንም ነጨው። የመቶ አለቃውና ባለጦሩ ከሕይወት ይልቅ ሞት ይገባሃል እያሉ ያንን ሊቀ ካህናት ይዘልፉት ነበር።
በአንድነት ከዘለፉትም በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት ሄዱ ወደ ንጉሥም ይወስዱት ዘንድ ተስማሙ።

የድንግል ማርያም በረከት የተወዳጅ ልጅዋም ምሕረት ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ይደርብን አሜን።