Get Mystery Box with random crypto!

ዱዓሽ ዱዓዬ ነው የሆነ ጊዜ አለኝ...ውስጤ ሁካታ እና ጫጫታ የሚበዛበት..የጭንቅላቴ እና የልቤ | ኹሉድ ✍️

ዱዓሽ ዱዓዬ ነው

የሆነ ጊዜ አለኝ...ውስጤ ሁካታ እና ጫጫታ የሚበዛበት..የጭንቅላቴ እና የልቤ ጦርነት ሰላሜን የሚነሳበት..ስሜቴን ለማስረዳት ፈልጌ ቃላቶች ባምጥ መውለድ የሚያቅተኝ..መሳቅ ፈልጌ ከናፈሬን መግለጥ የሚከብደኝ..ሰው ማናገር እንደ ዳገት የሚያደክመኝ ጊዜ አለኝ እናም በዛ ግራ በተጋቡ ስሜቶቼ ወቅት ሁለት ነገሮችን አዘውትሬ እጠቀማለው....አንድ..ዝም ያለ በአረንጓዴ የተሞላ መናፈሻ ውስጥ በጆሮዬ ላይ Earphoneን ሰክቼ ከራሴ ጋር ንግግርን  የምገጥምበት መድረክ ገንብቼ ከራሴው ጋር እሟገታለሁ..ሁለተኛው..መስጂድ ውስጥ ከሶላት በኋላ ሁሉም ሰዎች ሲወጡ ብቻዬን ቀርቼ ቁጭእላለሁ..ስሜቴን ማስረዳት መለመን ስለሚያቅተኝ አንተው ውስጤን አንብብልኝ እና ውስጤን አስክንልኝ ብዬ ተደፍቼ አነባለሁ። በዚህ ሰሞን በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነበር...እናም በዚኛው መስጂድ መሄድን ነበር የመረጥኩት...ሰዓቱ ከዝሁር በኋላ ስለነበር ሰው አይኖርም ብዬ ስገባ አንዲት ሴት ጥግ ጋር ተደፍታ ጌታዋን ትማፀናለች..እኔም አንዱ ጥግ ጋር ቁጭ አልኩ የልጅቷ ድምፅ እየጨመረ መጣ የምትለምነው በሙሉ ለኔ መሰማት ጀመረኝ...
"የተወደድከው አላህ ሆይ,
.እባክህን በገዛ እራሴው ልብ እንዳታሰቃየኝ ስል እለምንሃለሁ..እኔ ፍፁሟ ባርያክ አይደለሁም..ውድቀቶቼ፣ ኃጢአቶቼ እና ስህተቶቼ አጨማልቀውኛል ግን አላህዬ እወድሃለሁ አይደል?ስለዚህ እባክህ ልቤን ተመልከትልኝ.. በህመም ላይ ነው...ለማይፈልገው ሰው ከመጠን በላይ ፍቅርን ተሸክሞ ከመጠን ባለፉ ስሜቶች እየተሰቃየ ነው..
ፍቅር ፈውስ መሆን አለበት አደል እንዴ የእኔ ሁኔታ እንዴት ስቃይን ወለደ እእእ? ጌትዬ እባክህ፤ ይቅር በለኝ ልቤንም ማረኝ ስል ወደአንተ ዱዓን አደርጋለሁ..
የእኔ ያልሆነን ነገር በመውደድ ለኔ ያልተፃፈልኝን ነገር በመሻት ልቤን እንዳሰቃየው አትፍቀድልኝ....
ለረጅም ጊዜ ጠንካራ ሆኛለሁ.ብዙ ነገሮችንም መቻል እችላለሁ..ግን ይሄን...?!! አልችልም.."
ስቅስቅ ብላ ታነባለች.. "አሚን ያረብ ዱዓሽ ዱዓዬ ነው እናቴ" ብዬ ሳታየኝ ቀስ ብዬ ወጣሁ..ህመሟ  ተሰማኝ እኔ ያለሁበት ስሜት ስለሆነ ነው አደል? አዎን..ታድያ የጭንቅላትሽ እና የልብሽ ጦርነት መንስኤው ምን ሆነና..?ለራሴ ጠይቄ እራሴ መለስኩት..ቃል ያጣሁለት ስሜቴን ቃላቶችን ገጣጥማ ያስረዳችልኝ ያህል ተሰማኝ ውስጤ ቅልልል ሲለኝ ተሰማኝ...ቀና አልኩ እና ኧረ አሚንን ያረብ ለኔም ለሷም ብዬ ፈገግ አልኩ

ኹሉድ