Get Mystery Box with random crypto!

-- መንበር (Apostolic See. Or Holy See) -- ብርሃኑ አድማስ የመንበር ጉዳይ ገነ | JUSTIN APOLOGETICS]

--
መንበር (Apostolic See. Or Holy See)
--
ብርሃኑ አድማስ የመንበር ጉዳይ ገነን ብሎ የወጣው ከጉባኤ ኒቅያ ወዲህ ነው፤ ከዚያ በፊት ሐዋርያትም ሆነ ተከታዮቻቸው በመካከላቸው የሀገረ ስብከት ወሰን /jurisdiction/ አልነበራቸውም ነበረ ይላል፡፡ የመንበሮች ስያሜ ክርስትናው ወደ ሀገር ከገባበት ወይም በሀገሪቱ ላይ ካለው ገናና ቅዱስ ጋራ ይያያዛል፡፡ ሮማውያንና አንጾኪያዎች መንበራቸውን ‹‹መንበረ ጴጥሮስ›› ይሉታል፣ ሕንዳውያን ‹‹መንበረ ቶማስ››፣ ግብጻውያን ‹‹ምነበረ ማርቆስ››፣ አርመናውያን ‹‹መንበረ በርተሎሜዎስ››፣ በኢየሩሳሌም ያሉ ክርስቲያኖች ‹‹መንበረ ያዕቆብ፣ ብዙኃን የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ‹‹መንበረ እንድርያስ››፣ … ሁሉም የራሱን ከታሪኩና ከመንፈሳዊ ሕይወቱ የተገናኘ ስያሜ ይሰጣል፡፡ የኢኦተቤክ ቀደም ሲል ‹‹ማርቆስ አባታችን፣ እስክንድርያ እናታችን›› ማለቷ ለብዙ ጊዜ በእልህና በስሜት እንደምናስተሐቅረው ሳይሆን የአባቶቻችንን የሐዋርያዊ ክትትልንና የመንበር አንድነትን ትርጕም ማወቅ ያሳያል፡፡ በጊዜው ጊዜ ራሳቸውን ሲችሉ መንበሩ ‹‹መንበረ ተክለ ሃይማኖት›› እንዲባል ከግብጻውያን አበው ጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የመንበር ስያሜን ከሐዋርያዊ ክትትል አለመማምታታት ይገባል፤ ቢዛመዱም ልዩነት አላቸው፡፡ የአቡነ ባስልዮስ የፕትርክና ሹመት ከግብጻዊው ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ 6ኛ የተገኘ ነው፡፡ አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ደግሞ ከጌታ በንፍሐት ያገኘውን በአንብሮተ ዕድ ቅዱስ ጰየጥሮስ ካስተላለፈለት ወንጌላዊው የጌታ ረድዕ ቅዱስ ማርቆስ ጀምሮ ሲቈጠር 116ኛው በአንብሮተ ዕድ የተሾሙ አባት ናቸው፡፡ ስለዚህ የአቡነ ባስልዮስ ሥልጣን ወደኋላ ሲቈጠር የአንብሮተ ዕድ ንብርብሩ ጌታ ዘንድ ያደርስናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ሐዋርያዊት›› መባሏ ለዚህ ነው፡፡ ያለዚህ ክትትል ሐዋርያዊት መሰኘት እንደማይገባ በክብረ ክህነትና በምሥጢራት የሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ይስማሙበታል፡፡ ወደ ነገረ መንበር ስንመለስ፡- ክርስቲያኖች በቁጥር አናሳና የተጨቆኑ ካልሆኑ በቀር መንበር ብዙ ጊዜ ማዕከሉ በዋና ከተማ በሀገሪቱ መናገሻ ነው የሚሆን፡፡ መንበረ ፕትርክና/ ሊቀ ጵጵስና ይባላል፡፡ የግብፅ በታሪክ በእስክንድርያ (በእርግጥ እስክንድርያም ታላቅና ታሪካዊት ከተማ) ናት ቢባልም ፓትርያርኩ የሚቀመጡ በዋና ከተማዋ በካይሮ ነው፣ የምሥራቃውያኑ ታሪክ በዋና ከተማነት ባገነናት በቁስጥንጥንያ ናቸው፣ የካቶሊካውያን በሮም ነው፣ የእስራኤል በኢየሩሳሌም ነው፣ የራሽያ ኦርቶዶክሱ በሞስኮ ነው፣ … መንበሩ ከሚያገለግለው ሕዝብ መካከል ይሰየማል፡፡ ዐላማው ከተሜነትን ፍለጋ ሳይሆን በድካም ያሉትን ሰብአ ዓለምን መፈለግን ታሳቢ ያደርጋል፤ የአገልግሎት ተደራሽነትንና የተልእኮ መፋጠንንም ከግምት ያስገባል፡፡ በታሪክ የምናውቃቸው ታላላቅ አበው፡- ቀሌምንጦስ ዘሮም፣ አትናቴዎስ አዘስክንድርያ፣ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ፣ ቅዱስ ዮሐንስ (አፈወርቅ) ዘቁስጥንጥንያ፣ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ፣ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፣ … ከስማቸው ቀጥሎ የሚቀጸሉላቸው የቦታ ስሞች ሁሉ ታላላቅ ከተሞችና መናገሻዎች መሆናቸው ነገራችንን ያፀናልናል፡፡ ወደ ጵጵስና ከመጡ በኋላ ባለቅኔው እንዳለው ‹‹መንኖ ዓለም ዘምስለ ዓለም - በዓለም እየኖሩ ዓለምን መናቅ›› እንጂ የአገልግሎት ቆብ ከደፉ በኋላ በጸሎቴ ብቻ ነው የማገለግላችሁ ብሎ ከዋሻ መግባት አንድም ራስ ወዳድነት፤ አንድም መመጻደቅ ነው፡፡ የጴጥሮስ ሥልጣንን ከያዙ በኋላ በአደባባይ መስክሮ ማለፍ እንጂ መሹለክለክማ በሥልጣን ከቅዱስ ጴጥሮስ ያልተወለደ መጻተኛ መገለጫ ነው፡፡
--

የተፋልሶው አደጋ
--
የሐዋርያዊ ክትትል ዐላማ የሃይማኖት፣ የቀኖና፣ የሥርዓተ አምልኮና ሱታፌ ምሥጢር እንዲሁም መዋቅራዊ አንድነትን ማጽናት ነው፡፡ ይህ ዐላማ ሲፋለስ ዝርውነት ይከተላል፡፡ ምሥጢረ ክሀነትና በክህነቱ የሚከናወኑ ምሠጢራት ክብርና ተቀባይነት ያጣሉ፡፡ በክብረ ክህነት ከማያምኑ ተደምሮ መቈጠርን ያስከትላል፡፡ በራስ ጊዜ ተወግዞ መለየትን ይጋብዛል፡፡ ‹‹ዘወሐቦሙ ሥልጣነ ለሐዋርያት …›› እያሉ መናዘዝን፣ ‹‹በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ …›› እያሉ የማሰርና መፍታት ሥልጣንን ያሳጣል፡፡ ሥልጣናቸውን ከቀዳሚዎቻቸው መስመር ጠብቀው የተቀበሉ እንደ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ቄርሎስ፣ ዲዮስቆሮስ፣ … ያሉ አበውን ‹‹አባት›› ብሎ በሥልጣን የመጥራት መብትን ሐሳዊ ያደርጋል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዳለው የሐሳዊ መሲህን መምጣት መጠቆም ይሆናል፡፡ በጥቅሉ ኢሥርዓታዊነትን ያነግሣል፤ ምሥጢራትን ያራክሳል፤ ሕገ መጽሐፍን (መጽሐፍ ቅዱስን) ይጻረራል፡፡ አንድ አባት እንዳሉት ‹ይህን ሐዋርያዊ ክትትል ሰበሮ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ ማለት የጌታን እስትንፋስ እንደ ማቋረጥ፣ ለአንብሮተ ዕድ የተዘረጋ እጁን እንደ መቁረጥ ይቆጠራል፡፡› እንዲህ እናምናለን!
--
ወነአምን በ #አሐቲ #ቅድስት ቤተ ክርስቲን #እንተ_ላዕለ_ኵሉ ጉባኤ #ዘሐዋርያት፡፡
ደብተራ በአማን ነጸረ