Get Mystery Box with random crypto!

#ቃል #ዳንኤላ_ስቴል ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ ምዕራፍ አስራ አራት (14) ይህን ሐሳብ ግን | ✍ ልብ ወለድ በፅዮን ✍ fiction ❤️😘

#ቃል
#ዳንኤላ_ስቴል
ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ

ምዕራፍ አስራ አራት (14)

ይህን ሐሳብ ግን ልትገፋበት አልደፈረችም ። ይህ ሀሳብ በፊቷ ላይ ሲዳምን ፒተር አይቷል ። ብዙ ጊዜ ይጠብቀዋል ። እንድ የተጐዳችበት ነገር . . . ያለፈ ሕይወቷ ቁስል...
ቢሆንም በጊዜ ብዛት ልትረሳው ትችላለች ተስፋ ያደርጋል።
«ፊልምስ ? ፊልም አላመጣሀልኝም ? »
«አምጥቻለሁ እንጄ !» አለና አነስ ያለች አራት ማዕዘን ጥቅል እየወረወረላት ፤ «ካሜራ አምጥቼ ፊልም ልርሳ ?» ሲል ጠየቃት ። «አንተ !! አንተ ምንም አትረሳ !» አለችና መጣደፍ ጀመረች ፤ ካሜራውን ፊልም ለመሙላት ። ወዲያው በተለያዩ አቅጣጫዎች ፤ በተለያየ መንገድ ጠቅ ጠቅ ፤ጠቅ ፎቶ ታነሳው ጀመር ። ይህን እያደረገች እያለ አነስ ያለ ቁጥር ያላቸው ወፎች ባጠገባቸው ሲበሩ ቶሎ ብላ አነሳቻቸው ። «ምናልባት ደህና ፎቶ ላይወጣ ይችላል ። ግን ለመነሻ ምንም አይልም» አለች ። እሱ ግን በጽሞና ይመለከታት ነበር ። ለረጅም ጊዜ በዚህ ሁኔታ ሲያጤናት ከቆየ በኋላ ብድግ ብሎ አጠገቧ ቆመና እጁን ጣል አደረገው እትከሻዋ ላይ ። ከዚያም «ናንሲ ዛሬ ላበረክትልሽ ያቀድኩት ሌላም ስጦታ አለኝ» አላት ። «ገባኝ አወቅኩት ፤ መርሰድስ ነው አይደል?» «የለም ናንሲ ፤ አሁን እውነቴን ነው» አለና በለስላሳ የጽሞና ፈገግታ ተመለከታት ፤ ካንዲት ጓደኛዬ ጋር ላስተዋውቅሽ እፈልጋለሁ ፤ የሁለታችንም ጓደኛ እንድትሆን ። ለየት ያለች እመቤት ነች»

አንዳንድ ቅጽበት አለች ። የምናስበውን በቅጡ መረዳ? የማንችልባት ። በዚያች ዓይነቲቱ ቅጽበት ናንሲን የሆነ ቅናት መላ አካሏን ሲወርራት ተሰማት ። ቢሆንም ከፒተር ሁኔታ/ ስሜት ሊሰማት እንደማይገባ ተረዳች ። «ፌ ትባላለች» አለ ፒተር ። «ሕክምና ያጠናነው ባንድ ነው ። ባሁኑ ጊዜ ፌ አሊሰን በምእራብ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙት ሳይኪያችሪሰቶች አንዷ ናት ።ምናልባትም በሀገሪቱ ሉ ከሚባሉት ታላላቅ የአዕምሮ ሐኪሞች አንዷ ልትሆንም ትችላለች ። በጓደኝነት መልክ ከሆነ ደግሞ ጓደኛ ሳይሆን ሁሉን ነገር የማለት ያህል ናት ።እንደምትወጂያት ተስፋ አለኝ ።»
«እና ?» አለች ናንሊ በመንፈሷ ውጥረትና የማወቅ ጉጉት ይታይባታል ።
«እናማ ብትተዋወቁ... ብታነጋግሪያት ደህና ይመስለኛል ። ማለት ነገሩን ከዚህ በፊት በመጠኑ ይሁን እንጂ ተነጋግረንበታል»
«ትንሽ የተዛባ ፤ ማለቴ መንፈሴ በቅጡ የተረጋጋ መስሎ አልታየህም ማለት ነው? » የመከፋት ድምጽ ነበር ። ይህን ስትጠይቀው ካሜራውን ወደ ጐን ቁጭ አደረገች ።
«አላልኩም ናንሲ ፤ በሁሉም በኩል ምንም እንከን የለብሽም ። ከቀን ወደ ቀን እየተረጋጋሽ ፤ ከቀን ወደ ቀን አዲስ እየሆንሽ እንደምትሄጂ አትጠራጠሪ ። ግን ደግሞ አስቢው ። ሌላው ቢቀር የሚያዋራሽ ፤ ከኔ ሌላ ሰው ያስፈልግሻል ። እኔ ፤ ሊሊና ግሬችን ብቻ በቂ አይደለንም ። ሌላ ሰው ያስፈልግሻል ወይስ አያስፈልግሽም ? » አለ ። መልሱን በልቧ ሰጠች ። አዎ አለች በልቧ ፤ያስፈልገኛል ። ያም ሌላ ሰው ማይክል፤ እሱ ብቻ ነው ።

«እንጃ ርግጠኛ አይደለሁም ። አስቤው አላውቅም» አለችው፡፡ «ከፌ ጋር ከተዋወቃችሁ በኋላ ለካ ታስፈልገኝ ኖሯል እንደምትይ ርግጠኛ ነኝ ። በጣም ደግና ሰው ወዳድ ፍጡር ናት። በዚያም ላይ ስላንቺ ሁልጊዜ ትጠይቀኛለች»
«ታውቃለች ማለት ነው? »
«ገና ነገሩ ሲወጠን ጀምሮ !» አለ ። ይህን ያለውም ናንሲን ለማግባባት አልነበረም ። እውነቱን ነበር ። ዶክተር ዊክፊልድና ማሪዮን ሂልያርድ ደውለው ያነጋገሩት ዕለት ፌ አሊሰን አብራው ነበረች ። ምክንያቱም ምንም እንኳ ናንሲ ይህን ማወቅ ባይኖርባት ፤ ፒተር ግራግሰንና ፌ አሊሰን በአካልም ግንኙነት አላቸው ። እንደ ፍቅረኞችም ናችው ጉዳዩ ግን በጣም የጠነከረ አልነበረም ። ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ያደርጉታል ። ከሱ ይልቅ ጓደኝነታቸው የጠነከረ ነው ። «ዛሬ ከቀትር በኋላ እመጣለሁ ብላኛለች ። ቡና እየጠጣን እንጫወታለን ። እንዴት ነው ! ቅር ይልሻል ?»
«አይ ቅር አይለኝም» አለች ፤ ምክንያቱም ቅር ይለኛል ብትልም ዋጋ አልነበረውም ። ያለቀለት ጉዳይ ነው ። ከዚያ በኋላ የወትሮዋ ናንሲን መሆን አልቻለችም ። ሁሉ ነገሯ ቁጥብ ሆነ ። የለም የሌላ ሰው በሷና በፒተር መካከል መገባት ምንም ደስታ ሊሰጣት አልቻለም ። ሦስተኛ ጓደኛ... ለዚያውም ሴት ፤ አልመስልሽም አላት ። የውድድርና የእምነት ማጣት ስሜት ዋጣት ።

ይህም የሆነው ከፌ ጋር እስኪተዋወቁ ፤ ፌን እስክታያት ነበር ። ፌ አሊሰን በተባለው ሰዓት መጣች ። አየቻት። ረጅም ፤ ቀጭን ፤ ነጣ ያለ ወርቅማ ፀጉር ያላት አጥንተ ሰፊ ሴት ነበረች ። ሆኖም ፊቷ ምንም ዓይነት ጭካኔ ወይም ክፋት አይታይበትም ። ይህም ሁሉ ሆኖ የናንሲ ልብ አላመነም። ጨዋታ ሲጀመር ፌ በቀላሉ ቀጠለች። ዓይኖቿ ሕያው ሲሆኑ ፈጥኖ የመገንዘብ ችሎታም ይታይባታል ። ቀልድ ሲመጣ ሰም ቀለድ ፤ ሲጠይቋት ለመመለስ ፤ የሳቅ ሰዓት ሲሆን ደግሞ ከት ብላ ለመሳቅ ተዘጋጅታ የምትጠብቅ ትመስላለች ። ልብ ብሎ ያያት ሰው ለቁምነገርና ጨዋታም ዝግጁ መሆኗን ሊገነዘብ ይችላል ። በቂ ቃላት ከተለዋወጡ በኋላ ፒተር ሹልክ ብሎ ወጣ ሁለቱ ይበልጥ እንዲጫወቱ ብቻቸውን እንዲሆኑ ። ያኔ ናንሲ ደስ ተሰኘች ። ከልብ ደስ ተሰኘች ።

ፌና ናንሲ ስለብዙ ነገር አወሩ ። ሺህ ጉዳዮችን አነሱ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በናንሲ ላይ ስለደረሰው አደጋ አላነሱም፡፡ ወዲያው ፌ ስላሳለፈቻቸው ነግሮች ቀስ እያለች ታጫውታት ጀመር ። ቁርጥራጭ አጋጣሚዎችን ከሕይወቷ ውጥንቅጥ እየመዘዘች ነገረቻት ። ናንሲም ሳታስበው ከሕይወቷ አካል ትንሽ ገለጥ እያደረገች በጨረፍታ አሳየቻት ። እየቆየች ከዚያ በፊት በተለይም ከማይክል ጋር ከመገናኘቷ በፊት ለማንም ሰው ነግራ የማታውቃቸውን ነገሮች ሁሉ ነገረቻት ። ስለ እጓለማውታን ማሳደጊያው አወጋቻት ። ይህም ለፒተር በነገረችው መንገድ ሳይሆን ፤ ማለት በቀልድ ሳይሆን የምር ይሰማት የነበረውን ትዘከዝክላት ጀመር ። ብቸኝነቱን ፤ ማን ነኝ ? ከየት መጣሁ ? ብላ ትጠይቀው የነበረውን ፤ ማን ለምን እዚያ ወስዶ ከተተኝ ? ትል የነበረውን ሁሉ ።