Get Mystery Box with random crypto!

#ቃል #ዳንኤላ_ስቴል ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ ምዕራፍ አስራ ሶስት (13) 'ማይክ ፣ ለመሆኑ | ✍ ልብ ወለድ በፅዮን ✍ fiction ❤️😘

#ቃል
#ዳንኤላ_ስቴል
ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ

ምዕራፍ አስራ ሶስት (13)

"ማይክ ፣ ለመሆኑ በቅርብ ጊዜ ፊትህን በመስታወት አይተኸው ታውቃለህ ? ማስፈራሪያ መስለሃልኮ! ማይክ እባክህ እምቢ አትበል። አንድ ነገር ልለምንህ››
«ምን?»
«እምቢ አትበል››
«እኮ ጠይቀኝ››
«በዚህ በመጭው እሁድ ቅዳሜ አንድ ቦታ ሄደን እናሳልፍ።» ሁሉም ፤ጓደኞቻችን ሁሉ ይምጣ ብለዋል። » ቤን ይሀንን ያለው ከልቡ ነበር። ይህ ደግሞ ለማይክል በደንብ ገብቶታል። ሆኖም አራሱን በአሉታ ነቀነቀ። «ቤን ደስ ይለኝ ነበር ። እውነት! ግን ይኸው እንደምታየው ነው ስራው፤ በተለይ የካንሳስ ሲቲ የገበያ ማእከል ጉዳይ። ሌላም አለ። ምን ዋጋ አለው ብለህ ነው። ምንም መልስ የማይገኝለት አርባ ሰባት ጥያቄ ሆነኮ። ትናንት ስብሰባው ላይ አንተስ ነበርክ አይደለምንዴ «እኔም ብቻ ሳልሆን ሌሎች ሃያ ሶስት ሰዎችም ነበሩ ። ታዲያ ያ ሁሉ ሰው እያለ አንተ ብቻህን ምን በወጣህ ነው ማይክ ? እስኪ አስበው! ትንሽ ማረፍ የለብህም እንዴ። ቢንስ ላንድ ዊክ ኤንድ! ወይስ ስራዬን ማንም እንዲነካብኝ አልፈልግም ባይ ነህ ?»

ይህ የመጨረሻው አረፍተ ነገር እውነት እንዳልሆነ ቤንም ይገባዋል። ያ ሳይሆን ሥራ ለማይክል መሸሻ መሸሸጊያው ስለሆነ ነበር። ሥራ ማደንዘዣው ፤ ከሀሳብ መገላገያ መድሀኒቱ በመሆኑ ነበር። «እባክህን እሺ በለኝ ማይክ። ያሁኑን ብቻ ። ላንድ ጊዜ ብቻ››
«አልችልም ስለማልችልኮ ነው። ወድጄ አይደለም፤ ቤን»
«ሥራ!» አለ ቤን በጩኸት «ሥራ!... እንዲህ ከሆነ አፈር ድሜ ይጋጥ ፤ ፊትህን በመስታወት እየው አልኩህ !ከዚህ የበለጠ ምን እንድልህ ትፈልጋለህ ? ! ሌት ተቀን ሥራ ሥራ እያልክ ከሰውነት ጎዳና ወጣህ አልኩህ ። ከዚህ የበለጠ ምን እንድልህ ትፈልጋለህ ? ማይክ ስነግርህ ለምን አትሰማኝም? ይኽኮ ታንቆ የመሞት ያህል ነው። ለምኑ ነው እንዲህ እምትሆነው ? ሥራ ትላለህ እንጂ ደሞ እውነቱን ሁላችንም እናውቃለን። ይመን አይመን ሴላ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው ያውቀዋል ።»

ትንፋሹን ውጦ በኃይል ከተነፈሰ በኋላ እንደገና በሀይለ ቃል ቀጠለ ። «ማይክ ትወዳት ነበር ፤ አውቃለሁ ። እኔም ላስባት እንኳ አልፈልግም እንኳን አንተ ። ግን አስበው ። እሷ አንዴ ቀረች፤ አንዴ አለፈች። ምንም ማድረግ አይቻልም ። አንተ ግን አለህ ይኸው ! በሕይወት አለህ ። ጤናማ የሃያ አምስት ዓመት ጎልማሳ ! ታዲያ የተረፈውን ሕይወትህን እንዲሁ ልታስቀረው ትፈልጋለህ ? አመድ ልትነሰንስበት ትሻለህ እንደ እናትህ ሥራ ሥራ እያልክ ፤ ለፈጠርከው የገንዘብ መንግሥት ፤ወይም ለተቀበልከው ስውር መንግሥት አገልጋይ ሆነህ ልትቀር ብቻ ትፈልጋለህ ? አይገባኝም ፤ ማይክ ። አልቀበልህም ። ይህ አካልህ ያው ይምሰል እንጂ እማውቅህ እምወድህ ሰው አይደለሀም ። የማውቀውን ፤ የምወደውን ሰው ሌላ የማላውቀው ሰው ድቡሽት ሲጭንበት እያየሁ ነው።ይህን ደግሞ አልቀበለውም ። ወጣ በል። ለመኖር ሞክር። ከዚህ ከቅርብ እንጀምር ። ከቆንጆ ፀሐፊህ ጋር ውጣ ። ወይም በየፓርቲው በቀን መአት ቆነጃጅት ማግኘት ይቻላል ። ወይም... »

« ውጣ!» አለ ማይክ ከጣራ በላይ ጮሆ አቋርጦት «ውጣልኝ ቤን! . . . ከቢሮዬ ውጣልኝ ። ሳላንቅህ ፤ ሳልገልህ ውጣልኝ !» ከመቀመጫው ተነስቶ ፤ጣቶቹን ለማነቅ አንጨፍርሮ በጠረጴዛው ላይ ሰውነቱን አስግጎ ነበር እንዲህ ያለው ። ጩኸቱ የቆሰለ አንበሳ ጩኸት ነበር ። ለቅጽበት ያህል ሁለቱም ጓደኞች ተፋጠው እያሉ በያሉበት ቆመው ቀሩ ። ሁለ ቱም ስለተናገሩት ነገር ፤ በመካከላቸው ስለተፈጠረው ሁኔታ ሲያሰቡ ደንግጠው ፈርተው ነበር ። «ኦ ይቅርታ አድርግልኝ ቤን » አለና ተቀመጠ ። እና ራሱን በእጆቹ ደግፎ አቀረቀረ ። እዚያው እንዳቀረቀረ ቆይቶ ቀና ሳይል ፣ «ለምን አንተወውም ። ይለፍ ሌላ ቀን» አለ ማይክ ። ቤን አቭሪ ቃል አልተነፈሰም ። ቀስ ብሎ የቢሮውን በር ከፍቶ ወጣ ። ሲወጣ እንኳ ማይክ ቀና ብሎ ሊያየው አልቻለም ። በሩን ዘግቶ ሔደ ቤን። ሌላ የሚባል የሚጨመር ነገር አልነበረምና ምን ምን ሊል አልቻለም ።

ያን ለት ቤን አቭሪ ከቢሮው የወጣው በሥራ ሰዓት ላይ አንድ ሰዓት ተኩል ጨምሮ ነበር ። ከምሽቱ አሥራ ሁለት ተኩል ላይ ከቢሮው ሲወጣ የማይክል ቢሮ መብራት እንደበራ ነበር። ገና እስከምሽቱ አምስት ሰዓት ድረስ ያ መብራት እንደማይጠፋ ቤን ተገነዘበ ። እውነት አለው ። የት ይሂድ ? ወደቤቱ እሚሔድበት ምን ምክንያትስ አለው ? ከሶስት ወር በፊት ማይክል የተከራየው አፓርትማ ባዶ ነው። ሁለት ታጣፊ ወንበሮች ፡ ፡ አንድ አልጋ ሌላ ምንም ዕቃ የለበትም ። ቤን ያ አፓርታማ በሆነ መንገድ የናንሲን የቦስተን አፓርትማ እንደሚመስል ተገንዝቧል ። ማይክም ይህን ሳያይ አይቀርም ። ምናልባትም የተከራየው ያን ስላየ ይሆናል ። ግን ዋጋ የለውም ። ቤቱ ቤት ሊመስለው አልቻለም ። ኑሮው ኑሮ ሊሆንለት አልቻለም ። ስለዚህም እሥራው ላይ ተደፍቶ መዋል ፤ ማምሸት አመጣ ። እንደ እብደት ሥራ ሥራ ሥራ አለ ። ካልደከመው እንቅልፍ ሊወስደው ስለማይችል ይሆናል ።

ይህ ነገር ቤንን ደስ ሊያሰኘው አይችልም ። ሆኖም እሱም ሆነ ሌላ ሰው ምንም ማድረግ አይችልም ። ማንም ሰው ማይክልን ሊያድነው ፤ ከገባበት ማጥ ጎትቶ ሊያወጣው አይችልም ። ያለ አንድ ሰው በስተቀር ። ያለ ናንሲ በስተቀር። ናንሲ ደግሞ የለችም ። ናንሲ ደግሞ ቀርታለች ። ሞታለች ። ቤን ስለናንሲ ሲያስብ መላ አካሉን ስቅቅ አለው ። ሆዱን አመመው ። ቢሆንም የሱ የአካልም ሆነ የመንፈስ ቁስል እየሻረለት ነበር ። ወጣት ነውና እየሻረለት ነበር ። ምነው የማይክልም ቁስል እንደሱ ቁስል ቢሽር? ነገር ግን የማይከል ስብራት ድርብ ነው ፤ የነፍስና የሥጋ ሥብራት

«እሺ ወጣቷ እመቤት ? እንዴት ነው ቃሌን የምጠብቅ ሰው ነኝ ወይስ አይደለሁም ? ቤቱ እንዴት ነው ? ውበትን ለማሳየት ታቅዶ የተሠራ አይመስልሽም ?» አለ ፒተር ግሬግስን ግሬግሰን ይህን የሚለው ለናንሲ በተከራየላት አፓርታማ መናፈሻ ሰገነት ላይ ተቀምጠው የአካባቢውን ትዕይንት በማየት ላይ እንዳሉ ነበር ። ይህን ሲል መለስ ብላ አየችው። እሱም አያት በመተያየት ሐሳባቸውን ተለዋወጡ ። የናንሲ ፊት አሁንም በፋሻ እንደተጠቀለለ ሲሆን ዓይኖቿ እፋሻው መሐል በደስታ ሲጨፋፍሩ ይታያሉ። የእጅዋ ላይ ፋሻ ተፊትቷል ምንም እንኳ የከዚህ በፊቱ እጆቿን ባይመስሉም ውብ ነበሩ ። አፓርትመንቱ ፤ እመናፈሻ ሰገነቱ ላይ ሆኖ ማታ የፀሐይን መጥለቅ ፤ ጥዋት የፀሐይን መውጣት ለማየት እንዲያመች ሆኖ የተሠራ ሲሆን ይህ ደግሞ ለናንሲ ወሰን የሌለው ደስታን ሰጥ ቷት ነበር ። ፒተር እንደፎከረው ከሁሉም የተሻለውን አፖርታማ አገኘላት ። ይህን ስታስብ «ታውቃለህ ፒተር፣ አንዳንዴ እንደኛየን ሙልቅቅ አልኩኮ እያልኩ አስባለሁ» አለች ።

«ሲያንስሽ ነው ። ይልቅስ? አንድ ነገር አስታወስሺኝ ።. አንድ ዕቃ አምጥቼልሻለሁ» አለ ፒተር ገና ዕቃ እንዳመጣላት ሲናገር እንደሕፃን ልጅ መፈንጠዝ ጀመረች ፒተር አየት አድርጓት ፊቱ በደስታ እንደበራ ወደ ቤት ገባ ። ናንሲ ስለፒተር አሰበች ። ደግ ሰው ነው ። ትወደዋለች ምን ጊዜም ቢሆን የሚያስደስታትን ነገር ሲያድን የሚውል ይመስላታል ። የማይሰጣት ስጦታ የለም። እንደልጅ ያጫውታታል የመጽሔት ክምር ፤ የመጸሕፍት ቁልል ፤ አስቂኝ አሠራር ያለው ባርኔጣ ፤ ወደር የሌለው ያንገት ልብስ ያበረክትላታል ። እጆቿን ጠግኖ ፋሻውን ሲፈታ ላዲሱ እጅዋ መመረቂያ የሚያማምሩ አምባሮች ሰጣት ።