Get Mystery Box with random crypto!

#ቃል #ዳንኤላ_ስቴል ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ ምዕራፍ አስራ አንድ (11) ማይክል ማስተዛዘኛ | ✍ ልብ ወለድ በፅዮን ✍ fiction ❤️😘

#ቃል
#ዳንኤላ_ስቴል
ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ

ምዕራፍ አስራ አንድ (11)

ማይክል ማስተዛዘኛ ቃሉን ተቀብሎ መንገዱን ቀጠለ። ወደ አውራው መንገድ እየተጓዘ አሰበ ። እነማን ናቸው ? ነርሶቹ ከሆስፒታል የተላኩ ይሆኑ? ጥንብ አንሳዎች ! ጥሪት ለመለቃቀምማ ማን ብሏቸው! ምናልባት. . . ግን ምን ያገኛሉ ? ሥዕሎቿን ? እና ጥቂት ጌጣ ጌጦች እና. . . ጥንብ አንሳዎች !ምነው .. . ምነው ሲለቃቅሙ በያዝኳቸው ኖሮ ! ወይኔ ! ቀኝ እጁን ጨብጦ የግራውን መዳፍ በቦቅስ ነጠረቀውና በቡጢ በተመታው እጁ ጥብቅ እድርጐ ይዞ አሸው ። ድንገት ለቀቀውና ቡጢ የነበረውን እጁን ታክሲ ሊያስቆም ዘረጋው መጠንከሩ አይከፋም ። ምናልባት የሆነ ፍንጭ . . . ልሞክር. . . ፊቱ ላይ መጥቶ ቆመ ታክሲው… በሩን ከፍቶ ገባ ።

«በዚህ አካባቢ ያለው የጉድዊል ቅርንጫፍ የት ነው? » አለ ማይክል ።
«ጉድ ዊል ምን? .. . »
«ጉድ ዊል ዕቃ ማከማቻና መሸጫ. . . አሮጌ ልብስ... አሮጌ የቤት ዕቃ ምናምን…»
«ገባኝ »ገባኝ »

ጉድዊል ያገለገሉ ዕቃዎች ማከማቻና መሸጫ መደብር ሊገባ ሲል እውነት ምን ለማድረግ ነው የመጣሁት ? ዕቃዎቹ በጠቅላላ ቢኖሩስ ምን ለማድረግ ? አጠቃላዩን ልገዛ ? ከዚያስ ? ግራ ገባው ። ሊመለስ ከጀለ ። ግን አላደረገውም ። ወደ መደብሩ ውስጥ ስተት ብሎ ገባ ። ወጣ ወረደ ። አንድም ዕቃ ፤ የሷ የነበረ ነገር አላየም ። ግራ ገባው ። እንደገና አሰሳውን ጀመረ ወዲያው አንድ ነገር ብልጭ አለለት ። ለካ ለዕቃዎቹ ደንታ የለውም ! ለካ የሚፈልገው ዕቃ ሳይሆን ሰው ኖሯል ። እራሷን ? ናንሲን! አፓርታማውን እንዳለ ፣እንደነበረ ቢያገኘውም ለካ ጥቅም አልነበረውም ። ለካ ይኸ ሁሉ ልፋት ከንቱ ሽሽት ነበር ።

ከመደብሩ ወጣ…. ባዶ ሆኖ ሙት ሆኖ እንደህያው የሚንቀሳቀስ ሙት ሆኖ ወጣ። ታክሲ አልያዘም ። እንዲያ እሚባል ነገር ከነመኖሩም ለማስታወስ የሚችልበት አእምሮ አልነበረውም ። በዘፈቀደ መንገዱን ተያያዘው ። ግን ይህም ይባል ዘንድ ልክ አይመስልም ። ምክንያቱም በእግር ለመጓዝ ኃይል ያስፈልጋል ። አካል ፤ ሥጋ ፣ ኃይል ይፈልጋል ። ። አካሉ አጥንት አልባ የሆነ ለስላሳ ሆኖ ተሰማው ። ነፍሱ ግን ጠንካራ ነበረች ። ቆመ ግን ድንገት አልነበረም ። መንገድ ማቋረጥ ነበረበትና አረንጓዴው መብራት ጠፍቶ ቆዩ መብራት እስኪበራ ለመጠበቅ ቆመ ፤ ግን እስኪበራ አልጠበቀም ። የመጣው ይምጣ ብሎ ለመራመድ ሲሞክር ሰማይ ምድሩ ጨለመበት… ባዶ ።

ሲነቃ ሰዎች ከበውታል ። ከመንገድ አለፍ ብሎ በሚገኘው ሰው ሠራሽ መስክ ላይ ነበር የተንጋለለው ። ሰዎች ከበውታል ። ዓይኑን እንደገለጠ ፣
« ተሻለህ ፤ የኔ ልጅ» አለ አንዱ ፖሊስ
"ፖሊሱ ልጁን በደንብ ሲያጤነው ቆይቷአል ። ጠጥቶ እንዳልሰከረ ወይም አደንዛዥ እፅ እንዳልወሰደ ፤ ወይም ተደባድቦ አደጋ እንዳልደረሰበት ተረድቷል ። ህመም መሆኑን አውቆታል።
“ደና ነኝ» አለ ማይክል ረሀብ ይሆን? አለ ፖሊሱ በሀሳቡ ። ደግሞ ይህን ሀሳብ ለመቀበል አስቸጋሪ ሆነበት። ልጁ በደህና እንክብካቤ ያደገ ይመስላል ። የተጎሳቆለ ነገር አይታይበትም ።
«ያውቅሀል ፤ ከዚህ በፊት?»
«አይ ፤ ትንሽ ስላመመኝ... ዛሬ ነው ከሆስፒታል የወጣሁት። እኔም ትንሽ አበዛሁት መሰለኝ » ማይክል እዚያው እንደተጋደመ የከበቡትን ሰዎች አየ ። ሙሉ ክብ ሰው። ቀና ሊል ሲሞክር ከሰዎች የተሰራው ክብ እንደመንኮራኩር መሽከርከር ጀመረ ። ተመልሶ ተዘረጋ ይህን የተመለከተው ፖሊስ ሰዉን በተነና ተመልሶ
«መኪና ይመጣልሀል ። ለጥበቃ የተሰማሩ መኪናዎች አሉ፤ እናደርስሀለን» አለ ።
«አይ ይህን ያህልም… »
«ግዴለም» ፖሊሱ ይህን ብሎ ባጭር ርቀት መነጋገሪያ ሬድዮው መልእክቱን አስተላለፈ ። መኪናው ካካባቢው አልራቆ ኖሮ ወዲያውኑ ከች አለ።
ማይክል ተሳፈረ። ከሆቴሉ አንድ ምዕራፍ ያህል መለስ ያለ አድራሻ ሰጣቸው ። የተባለው ቦታ እንደደረሱ አወረዱት።
«አይዞህ» አለው ፖሊሱ ።
«እግዜር ይስጥልኝ » ሆቴሉ ሲደርስ ማንም አልነበረም ። ቀድመውት አልደረሱም ማለት ነው ። ልብሱን አወላልቆ አልጋው ላይ ወጥቶ ሊተኛና ሊጠብቃቸው አሰበ ። ግን ወዲያው ሐሳቡን ሰረዘው ምን ዋጋ አለው? ምን ድብብቆሽ መጫወት ያስፈልጋል ? ሊያደርገው ያሰበውን እንደሆነ አድርጓል ። ምንም እንኳ ከእውነቱ ፈቀቅ ሊያደርገው ባይችል ቁርጥ ማወቅም ደግ ነው ። ናንሲን ነበር የሚፈልገው ። ናንሲን አላገኛትም ። ሊያገኛት እንደማይችል ቀድሞውኑ መገንዘብ ነበረበት ። ዛሬም ፣ ወደፊትም ፤ የትም የት ሄዶ መፈለግ የለበትም ። ፍለጋው ፋይዳ ቢስ ነው። ግን ናንሲ ሁልጊዜም አለች። ያለችውም አንዲት ቦታ ነው ። ልቡ ውስጥ ፤ እራሱ ማይክል ውስጥ… በቃ!

የክፍሉ በር ሲከፈት ይህን እያሰበ እመስኮቱ አጠገብ ቆሞ ወዲያን ይመለከት ነበር ። ወደ ውጭ። ወዲያ በጣም ወዲያ።
«ምን ትሰራለህ እዚያ ጋ ማይክል?» አለች ማሪዮን ሂልያርድ። ሁልጌዜ እንደ ሕጻን!ሃያ አምስት አመቴን ልደፍን እንደሆነ አንድም ቀን አትገነዘብም አለ በሐሳቡ ።
‹‹ከእንግዲህማ ይብቃኝ ፤ ማሚ» አለ ማይክል ። «ቀና ፤ ቀና እያልኩ ካልተለማመድኩኮ ተኝቼ መባጀቱ ነው። እንዲያውም ዛሬውኑ ኒውዮርክ ሄጄ ለማደር አስቤአለሁ »
«ምን አልክ?»
«ኒውዮርክ ለመሄድ አስቤአለሁ»
«ግን… እዚህ ትንሽ ቀን ለማሳለፍ እፈልጋለሁ ብለህ ነበረ ኮ!» ግራ የመጋባት ሁኔታ ይታይባት ነበር።
«ምን አደርጋለሁ!? በዚያም ላይ አንችም ስብሰባሽን ጨርሰሻል» አለና በልቡ ደግሞ እኔም ጉዳዬን ፈጽሜአለሁ ሲል ጨመረ ። ቀጥሎም «ስለዚህም መሄዱ ይሻላል ። እንዲያውም ነገውኑ በጧት ሥራ መጀመር አለብኝ። አይመስልህም ጆርጅ?» ብሎ ጆርጅን አየው ።

ጆርጅ ማይክልን በደንብ ካጠናው በኋላ ፣ ልጁ በሀዘን ተሰብሯል ። ምናልባት ሥራው ያፅናናው ፤ ያረሳሳው ይሆናል ሲል አሰበና
«ወርቅ ሀሳብ ነው» ሲል መለሰ። « ግን እስክትጠና ድረስ ግማሽ ቀን ብትሰራ በቂ ነው»
«አልገባኝም ። አበዳችሁ ልበል ወይስ..." ትናንት ከሆስፒታል ወጥቶ ሥራ…!» አለች ማሪዮን ።
«አቤት! አቤት!» አለ ማይክል ነገሩን ወደቀልድ እየለወጠ «አሁን እንዲህ ሲሉ እሳቸው ይረፉ ቢሏቸው በጄ እሚሉ አይመስሉም!» ይህን ብሎ «በያ መልስ ስጪ !» በሚል አስተያየት አያት። ቀስ ብላ እሶፋው ላይ አረፈችና ተደግፋ ተቀመጠች። «እሺ በቃ ይሁን ፤ አታፍጥብኝ» አለች ቀልዱ ደስ ብሏት ፈገግ እያለች ። ይኸኔ የንግግሩን ፈር እየቀየረ ፤ «ስብሰባው እንዴት ነበር?» ሲል ጠየቀ ። ፈር መቀየሩ ብቻ ሳይሆን ካቀዳቸው ነገሮች መካከል ዋናውን መጀመሩ መሆኑን ወዲያው ተገንዘበ ። ዛሬ ለማይክል በአለም ላይ የቀረው ነገር ቢኖር ይኸው ነው ። ለመኖር ከፈለገ አሁን ሊሄድበት በጀመረው መንገድ ጭልጥ ብሎ መሄድ አለበት። ወሬው ሐሳቡ ሁሉ እድርጅቱና እሥራው ላይ መሆን አለበት። ጉልበቱ ፤ፍቅሩ ለድርጅቹና ለሥራው መሆን አለበት ። ሕይወቱ እሱ ብቻ ነው። ምን ቀረው? ከሥራው ውጭ ያለ ሕይወቴማ አበቃ ። አለቀ ። ከናንሲ ጋር ተቀበረ ።