Get Mystery Box with random crypto!

ሀንፃውን ቀና ብሎ አየው ፤ በፍቅር፤ በፈገግታ ። እና ከቁጥጥር ውጭ ሊባል በሚችል ሁኔታ በልቡ ያ | ✍ ልብ ወለድ በፅዮን ✍ fiction ❤️😘

ሀንፃውን ቀና ብሎ አየው ፤ በፍቅር፤ በፈገግታ ። እና ከቁጥጥር ውጭ ሊባል በሚችል ሁኔታ በልቡ ያሰበው ነገር ከአፉ ሲወጣ ድምፅ ሆኖ ተሰማው « ሃይ ፣ ታዲያስ !» አለ። ባለፉት ዓመታት ይህን ሺህ ጊዜ ደጋግሞ ብሎታል ። እዚህ ቤት ፤ ታዲያስ !»ይልና ከፍቶ ይገባል ። ያኔ ያያታል ፤እሸራ መወጠሪያ አትሮኑስዋ አጠገብ ቆማ ፤ ቀለም ተፈናጥቆባት ። እጅዋ ላይ እክንዷ ድረስ ፤ አንዳንዴም ፊቷ ሳይቀር በቀለም ተላብሶ ያያታል አንዳንዴ ስራዋ ላይ እያለች ከሆነ ሲገባም አትሰማ ። እንግዲህ አንደኛው ቁልፍ እሱ ዘንድ ነበር የሚቀመጠው። ስለዚህ ለመግባት ማንኳኳት የለበትም። ይህን እያሰበ በቀስታ ደረጃውን ወጣ ። በጣም ደክሞት ነበር። ሆኖም ለማረፍ አልከጀለም ። ሊያየው የፈለገው ነገር እየገፋ እያንሳፈፈ ሽቅብ ነዳው ።እዎ ማረፍ የለበትም፤፣መድረስ እለበት ። ከደረሰ በኋላ ሄዶ ፤ ከእስዋ ጋር … ከእሷ አጠገብ የእሷ ከሆኑ እቃዎች ፤ ከእሷ ንብረቶች አጠገብ መቀመጥ ብቻ ነው እሚፈልገው ። ያ ፍላጐት ነው ሽቅብ የሚነዳው፡፡ በስተውጭ ሁሉ ነገር እንደነበረ ነበር ። የቀለሙ ሽታ ሳይቀር ሸተተው ። ውሀ ሲቀዳ ይሰማዋል ። የሕፃናት ድምፅ ፤ የድመት ጩኸት ... ሁሉ ነገር ይሰማዋል። ያው ነው፣የተለወጠ ነገር አልነበረም ። ቆይቶ የጣልያንኛ ዘፈን ተሰማው…. ሬዲዮኑን አልዘጋችውም ማለት ነው? አለ በሃሳቡ ። ቁልፉን ከኪሱ እወጣና በሩን ለመክፈት ተዘጋጀ ። ይኸኔ እውነት ብቅ አለች ። ናንሲ የለችም! አላገኛትም አለ በሃሳቡ ። ናንሲ ሞታለች አለ በሃሳቡ ። አዎ ሞታለች ። ይህን መርዶ ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ ድምፁን ከፍ አድርጐ «ሞታሉች» ለማለት ደጋግሞ ሞክሮ ነበር ። ግን አልቻለም። ይህን የሞከረው ደግሞ በከንቱ አልነበረም ። ማይክል ሐቁን እየሸሹ ደግ ደጉን በማሰብ በተስፋ በውሸት ተስፋ ለመኖር እንደሚሞክሩ አንዳንድ ሰዎች መሆን አይፈልግም ። ስለዚህ እውነቱን ለመጋፈጥ ደጋግሞ ሞከረ ፤ ሞታለች ብሎ ለራሱ ሊነግር። ራሱን ሊያፅናና ግን አልቻለም ። ይህን ደካማነቱን ብታውቅበት እንዴት ትንቀው !ይኸ ሁሉ በሃሳቡ ነበር ። ግን ይረሳል ። ሞቷን ይረሳል ፤ ላይቀርለት ። ለቅጽበትም ያህል ቢሆን እውነቱ አካል ያወጣ ያህል ብቅ እያለ በጥፊ ማጠናገሩን ላይተው ። ልክ በዚህ ቅጽበት በሩን ሊከፍት ሲሰናዳ እንዳጮለው ሁሉ በየሰዓቱ ማጮሉን ላይተወው እውነቱን ይሸሻል።

ሰረገላውን ቁልፍ ካዞረና ከከፈተው በኋላ ቆም ብሎ ጠበቀ ምናልባት አንድ ሰው ከበስተውስጥ ይከፍትልኝ ይሆናል ብሎ ተስፋ ያደረገ ይመስል ጠበቀ ። ግን ማንም አልከፈተለትም ማንም ብቅ አላለም ። በሩን ገፋ አደረገው ። ወደ ውስጥ ተመለከተ ። እንደገና ከእውነቱ ራቀ። እና የተመሰጠች ፤ በስራዋ የተዋጠች ናንሲን ሊያይ ፈለገ ግን ያጋጠመው ሌላ ነበር፡፡ አንድ የሚያስደነግጥ ድምፅ ከትንፋሹ ጋር አስወጣ ። አስደንጋጭ የድንጋጤ ድምፅ።
«ኦ! አምላኬ. ! የታለ ? ወዴት ?» ሁሉም ነገር ባዶ ነበር። ሁሉም ነገር ። ጠረጴዛ የለ ፤ወንበር፤ ቀለም የለ ብሩሽ ፤ የሸራ መወጠሪያ አትሮኑስ የለ ቀለም ማደባለቂያ ፤ ቤት ውስጥ የበቀሉ አበቦች የሉ ፤ ምንጣፍ...አንድም ነገር አልቀረም ። ቤቱ ባዶ ...ወና ሆኗል ።
«የክርስቶስ ያለህ ! ናንሲ !» አለ አጠገቡ ያለች ይመስል፤ የት አደረስሽው ? ሊላት የፈለገ ይመስል ። የሌሎቹን ክፍሎች በር እየከፈተ ተራወጠ ፣ እንባው በፊቱ ላይ እንደ ጐርፍ እየወረደ ። ጨዉ ፊቱን ሲያቃጥሊው ተሰማው፡፡ አይኑን ሲቆጠቁጠው ተሰማው ። እንዲህ ሆኖ ነው ማልቀሱን እንኳ የተገነዘበው እንጂ እንባውስ ዝም ብሎ ነበር የወረደው፤ ፊቱን ያጠበው ።

የትም የት ምንም እቃ አልነበረም ። ባለበት ደንዝዞ ቀረ። ሃሳቡ ሁሉ ሙልጭ ብሎ ከአእምሮው ወጣ። ድንገት በሩን በርግዶ ወጣና ወደታች መውረድ ጀመረ።ሁለቱን ደረጃ ባንዴ እየተራመዶ ምድር ቤት የሚገኘውን የሕንፃውን ዋና አስተዳዳሪ ቢሮ ሲያይ ወደዚያው ሄደ። በቡጢ ይነርተው ጀመር ። ደቃቃው አስተዳዳሪ ደንግጦ በሩን ቀስ ብሎ ከፈተው ፤ በሩን የሚመታው ሰው አደገኛ መስሎ ከታየው መልሶ ለመዝጋት በመጠንቀቅ ። ግን ወዲያው አወቀው ። ማይክልን አወቀው ። ስለዚህም በሩን በደንብ ከፈተው ። ሆኖም የገመተው ማይክል ሳይሆን ቀረ። አንገቱን በሸሚዙ ሲያንቀው ደነገጠ ። ማይክል ሰውየውን አንቆ ይዞ እያርገፈገፈ
«የታለ ! . . እቃዋ ሁሉ የታለ !? እቃዋ ሁሉ የታለ ካውሰኪ ? የት ወሰድከው? የት ከተትከው?» አለ።
«የምን . . የምን እቃ? . .ኦ ! አምላኬ ! ገባኝ ። የለም ፤ የለም እኔ አይደለሁም ። አንዲት ስንጥር ነገር አልነካሁም ። ከአስራ አምስት ቀን በፊት . . አካባቢ... መጥተው ወሰዱት ። እና ደግሞ እንዲህ ብለው … » ሰውየው መንቀጥቀጥ ጀምሮ ነበር።
‹‹ማናቸው ? እነማን ናቸው እነሱ ?»
«አላወኩም። . . ብቻ ጠሩኝና ነገሩኝ ። ሚስ ማክአሊስትር...» ይህን እያለ ማይክልን ቀና ብሎ አየው ። ፊቱ በሐዘን ተውጦአል፡፡ አይኖቹ በእንባ ዳምነዋል ። ስለዚህም ሊናገረው የነበረውን ቃል ዋጠው።
«ያው ታውቃለህ አይደል ! በኋላ ነገሩኝ ። ከጥቂት ቀናት በኋላ እቃውን እናወጣለን አሉኝ ። እንዳሉትም ሁለት ነርሶች መጥተው አንዳንድ እቃዎችን ወሰዱ ። በማግስቱ የጉድዊል ጭነት መኪና መጣ። ሌላውን እቃ ሙልጭ አድርጐ ወሰደው። እኔ ...እኔ ምንም እቃ አልነካሁም ። አላደርገውም ። ያችን የመሰለች ልጅ…»
«ሰዎች ያልካቸው እነማን እንደሆኑ አታውቅም? ማለት ከየት እንደመጡ።
«ምንም አላወቅኩም ። ነጭ ልብስ ለብሰዋል ። ለዚህ ነው ነርስ የመሰሉኝ ። እነሱ የልብስ ሻንጣዋንና ስእሎቿን ብቻ ነው የወሰዱት ። ሌላው እቃ ወደ ጉድዊል ነው የተጫነው ። እኔ… እኔ አንድም ነገር አልነካሁም ። በፍጹም እኔስ ነገ ... ››

ግን ማይክል አይሰማውም ነበር ። አስተዳዳሪውን ትቶ ወደውጭ መውጣት ቀጠለ ። ሰውየውም እየውና በሀዘኔታ አንገቱን ነቀነቀ ። እና ድንገት
«ስማኝ ልጄ….» ሲል ተጣራ ። ማይክል መለስ ብሎ አየው ።
« ስለሆነው ሁሉ እዝናለሁ ፤በርታ » አለው።

ይቀጥላል......

ሀሳብ አስተያየታችሁን
@Tsiyon_awit
አድርሱኝ

ቻናላችንን ይቀላቀሉ
@itsmetsiyearsemalj
@itsmetsiyearsemalj